ጥቅምት 20 2018 - የፍትህ ስርዓት ችግር ምክንያት ስራው ላይ እክል እየገጠመው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ
- sheger1021fm
- 1 hour ago
- 1 min read
የሚሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦች ያለ በቂ ምክንያት የማይፈፅሙ ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ቢሞክርም ባለው የፍትህ ስርዓት ችግር ምክንያት ስራው ላይ እክል እየገጠመው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ፡፡
ተቋሙ የአስተዳደር በደል ደረሰብን እምባችን ይታበስልን የሚሉ አቤት ባዮችን ቅሬታ በመቀበልና በማጣራት እንዲሁም አስተዳደራዊ በደሎች መፈፀማቸውን ሲያረጋግጥ ማስተካከያ እንዲደረግ ለተቋማት ምክረ ሃሳቦችን ይሰጣል፡፡
ቅሬታ የቀረበባቸው ተቋማት አሰራሩ እንደሚፈቅደው በ1ወር ጊዜ ውስጥ ምክረ ሃሳቡን መፈፀማቸውን ወይም አለመፈፀማቸውን ከእነምክንያቱ ለእምባ ጠባቂ ተቋም ማሳወቅ እንዳለባቸው የተቋሙ ምክትል እምባ ጠባቂ የኔነህ ስመኝ (ዶ/ር )ነግረውናል።
ምክረ ሃሳቡን ተቀብለው ማስተካከያ የሚያደርጉ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ ያለ በቂ ምክንያት ለአቤት ባዮች ቅሬታ ምላሽ የማይሰጡ ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ የሚያነሱት ሃላፊው ይሁንና የእምባ ጠባቂ ተቋምን ምክረ ሃሳብ ያለመፈፀም ወንጀል በመሆኑ ለአቃቢ ህግ ክስ እንዲመሰረት ብንልክም ጉዳዩን እንደ ሌላ ወንጀል እንዲጣራ ወደ መርማሪ ፖሊስ የሚልኩት በመሆኑ ስራችን ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል የተቋሙን ምክረ ሃሳብ ለመፈፀም እምቢተኛ የሚሆኑ ተቋማት ላይ ልዩ ሪፖርት በማዘጋጀት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እርምጃ እንዲወስድ ያቀርባል የሚሉት ዶክተር የኔነህ ይህም ቢሆን አጥጋቢ አይደለም፤ ምክር ቤቱ ሪፖርቱን ተከትሎ እርምጃ መውሰድ ላይ ሊበረታ ይገባልም ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር እምቢተኞቹን ተቋማት በሚዲያ ማጋለጥ በቅርቡ የጀመርኩት ተግባር ነው የሚለው እምባ ጠባቂው ተቋም ይህኛው መንገድ ይበልጡን የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁና እቀጥልበታለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በባለፈው የ2017 በጀት ዓመት ከማህበረሰቡ 1137 አቤቱታዎችን የተቀበለ ሲሆን 670 ያህሉ በተለያየ መንገድ ውሳኔ አግኝተው አቤት ባዮች መልስ ያገኙበት መሆኑን የተቋሙ ሪፖርት ያሳያል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








