ጥቅምት 20 2018 - በሥራቅ አርሲ ዞን ባለንበት በጥቅምት ወር ብቻ 25 ሰዎች መገደላቸውን፣ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ተናገረ።
- sheger1021fm
- 5 hours ago
- 1 min read
በኦሮሚያ ክልል በሥራቅ አርሲ ዞን ባለንበት በጥቅምት ወር ብቻ 25 ሰዎች መገደላቸውን፣ ይህንንም የተመለከተው በከባድና ጥልቅ የኃዘን ስሜት መሆኑን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ተናገረ።
ቋሚ ሲኖዶስ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር በጉና፣ በመርቲ፤ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ ጥቅምት 14 ለ15 ቀን 2018 ዓ.ም በጉናና መርቲ ወረዳዎች 17 ሰዎች መገደላቸውን አስረድቷል ።
ጥቅምት 17 ለ18 ቀን 2018 ዓ.ም በሸርካ ወረዳ 3 እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ19 2018 ዓ.ም በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ 5 ሰዎች መገደላቸውን ቋሚ ሲኖዶሱ አሳውቋል።
በዚህም በድምሩ በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ብቻ 25 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ግድያው የተፈፀመውም አገራችንና ምድራችን ብለው በሰላም በተኙበት በድንገት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መሆኑን ቋሚ ሲኖዶስ ጠቅሷል።
ግድያውም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መሆኑን የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የላከውን ሪፖርት ቋሚ ሲኖዶሱ መመልከቱን በመግለጫው ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ግድያው በጽኑ ማውገዙን ከመግለጫው ላይ ተመልክተናል።
በመሆኑም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ተግባር በጽኑ በማውገዝና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና የእምነት ነጻነት መብትን እንዲያስከብሩ፣ ድርጊቱን የፈጸሙትን ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
ወደፊትም እንዲህ ዓይነቱ ሕገ ወጥ ተግባር እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቋሚ ሲኖዶሱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








