ጥቅምት 19 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 2 min read
የብራዚል ፖሊስ የሬዮ ዴ ጄኒየሮ ከተማን ከተደራጁ ወሮበሎች ለማፅዳት ባካሄደው ዘመቻ በጥቂቱ 64 ሰዎች ተገደሉ ተባለ፡፡
ከተማይቱ በቅርቡ አለም አቀፋዊ የአየር ለውጥ ጉባኤን እንደምታስተናግድ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
ፖሊስ ለዚህ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ሬዮ ዴ ጄኔሮን ከወሮበሎች ለማፅዳት በዘመቻ ላይ ነው ተብሏል፡፡

በአጋጣሚው በተፈጠረው ግጭት ከተገደሉ 64 ሰዎች መካከል 4ቱ የፖሊስ መኮንኖች መሆናቸው ታውቋል፡፡
በትናንቱ ዘመቻ 2 ሺህ 500 ፖሊሶች እና ሌሎች የፀጥታ ባልደረቦች መካፈላቸው ተጠቅሷል፡፡
በግጭቱ በፀጥታ ባልደረቦቹ እና በተደራጁት ወሮበሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
ፖሊስ ከ80 በላይ የተደራጁ ወሮበሎችን አስሬያለሁ ማለቱ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
በቤኒን የዋነኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር ከመጪው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ውጭ ተደረገ፡፡
የዋነኛው ተቃዋሚ እጩ በፕሬዘዳንታዊ ምርጫው እንዳይፎካከሩ የወሰነው የአገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት እንደሆነ አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
የእጩነት መመዝገቢያ ገንዘብ አልከፈሉም መባሉ የዋነኛው የተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር እጩ ከተፎካካሪነት ከተሰረዙባቸው ምክንያቶች አንዱ ነው ተብሏል፡፡
እርምጃው ከወዲሁ የምርጫውን ፍትሃዊነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ እየከተተው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ታዛቢዎችም በዚህ እርምጃ ስጋት ገብቶናል እያሉ ነው፡፡
ቤኒን ከዚህ ቀደም መልካም የዴሞክራሲ ክንውኖች የሚታይባት አገር እንደነበረች መረጃው አስታውሷል፡፡
የአፍጋኒስታን እና የፓኪስታን ሹሞች በቱርክ ኢስታምቡል ሲያካሂዱት በሰነበተው የሰላም ንግግራቸው በጭራሽ መግባባት አልቻሉም ተባለ፡፡
ሁለቱ አገሮች ከወር በፊት ወደ ወሰን ተሻጋሪ ቁርቋሶ አምርተው እንደነበር አረብ ኒውስ አስታውሷል፡፡
ፓኪስታን ጎረቤት አፍጋኒስታን የፓኪስታን ፅንፈኛ ታጣቂዎች ጥላ ከለላ ሆናለች ስትል በተደጋጋሚ ትከሳለች፡፡
አፍጋኒስታን ውስጥ የፅንፈኛ ታጣቂዎች ምሽጎች ናቸው ያለቻቸውን ስፍራዎች በጦር አውሮፕላኖች ስትመታ ቆይታለች፡፡
የአፍጋኒስታኑ ታሊባን አስተዳደር በበኩሉ በፓኪስታን ድብደባ ሰላማዊ ዜጎቼ እየተገደሉ ነው ሲል ይከሳል፡፡
የፓኪስታኖቹን ታጣቂዎች እኛ በፍፁም ልንቆጣጠራቸው አንችልም ባይ ነው ታሊባን፡፡
የኢስታምቡሉ የሰላም ንግግር ያለ ስምምነት ያበቃው በዚሁ ምክንያት እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የጋዛው የእስራኤል እና የሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እየሆነ ነው ተባለ፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጦራቸው በጋዛ ሰርጥ እጅግ ሀይለኛ ድብደባ እንዲፈፅም ማዘዛቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ኔታንያሁ የተቆጡት ሐማስ የሟች እስራኤላዊ ታጋች ነው ብሎ ያስረከበው አንድ አስከሬን የተባለው ሆኖ ባለመገኘቱ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም ሐማስ በተኩስ አቁም ስምምነቱ የገባውን ግዴታ አልተወጣም ሲሉ ኔታንያሁ ተናግረዋል፡፡
ሐማስ ግን የኔታንያሁን ክስ የአዲስ የጥፋት ዘመቻ ሰበብ ፈጠራ ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የኔታንያሁ የአዲስ ድብደባ ትዕዛዝ እንደተሰማ በጋዛ ነዋሪዎች ዘንድ ፍርሃት እና መሸበር ነግሷል ተብሏል፡፡
ሐማስ እስራኤል ራሷ በሀይል እርምጃዋ የሟች ታጋቾችን አስከሬን ፍለጋውን እያከበደችብኝ ነው ማለቱ ተጠቅሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ አስችያለሁ ቢሉም የተኩስ አቁሙ ከወሰድ መለስ እንዳልተላቀቀ መረጃው አስታውሷል፡፡
ከኔታንያሁ የጥቃት ትዕዛዝ በኋላ በጋዛ ሰርጥ በተፈፀመ የአየር ድብደባ በጥቂቱ 33 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments