ጥቅምት 18 2018 - መንግስት “ጽንፈኛ እና አሻባሪ” የሚላቸውን ቡድኖች ከመውጋት ባለፈ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ለምን እንደማይሰራ ተጠየቀ፡፡
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 2 min read
ጥያቄው የቀረበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ለመስጠት በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በተገኙበት ወቅት ነው፡፡
የአብን ፓርቲ ተወካዩ የምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች ክልሎች ያሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ተባብሰው በመቀጠላቸው ብዙዎችን እየጎዱ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ጽንፈኛ እና አሻባሪ የሚላቸው ቡድኖች ከሙውጋት ባለፈ ለሁለቱ ክልሎች ማለትም ለአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከወታደራዊ አማራጭ ውጪ የተለየ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ለምን እንደማይሰራ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የእርስ በእርስ ጦርነት አንገፍግፎታል፣ በአገር ውስጥ ተንቀሳቅሶ መስራት እና ሰርቶ መብላትም ከብዶታል ፣ አገራችንም እንደ ኮሎምቢያ 50 ዓመታትን እየተዋጋች ልትቀጥል አትችልም ሲሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
አቶ መለሰ መና የተባሉ የምክር ቤት አባልም ግጭቶች በአንድ አንድ ክልሎች እንደሚስተዋሉ አስታውሰው ነገር ግን መንግስት ባደረገው የሰላም ጥሪ ቀላል የማይባሉ ታጣቂዎች ጥሪውን ተቀብለው ወደ ህበረተሰቡ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ቢሆን የሰላም ጥሪውን ያልተቀበሉ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማዳከም ቀን ከለሊት የሚሰሩ አካላት አሉ ያሉት አቶ መለሰ በተለይ በአማራ እና አሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶችን በመግደል፣ ትምህርት ቤቶችን በማፍረስ፣ ህጻናት እንዳይማሩ በማድረግ የህዝብን አገልግሎት ተቋማት በማፍረስ ንጹሃን ዜጎችን በሚያግቱ እና የጭካኔ ተግባራትን ላይ የተሰማሩ ሃይሎችን ለመቆጣጠር ምን እየተሰራ እንዳለ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ጫላ ለሚ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ሕውሃት ከሌሎች ሃይሎች ጋር በመሆን ዳግም ጦር እየሰበቀ ነው ሲሉ ከከሰሱ በኋላ ይህን ቡድን አደብ ለማስገዛት ምን እየተሰራ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤት አባሉ አሁን በትግራይ ክልል ስላለው የሰላም እና የፖለቲካ ሁኔታም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግጭቶችን በተመለከተ የተነሱ ስጋቶች ትክክለኛ መሆናቸውን አስታውሰው ግጭቱ ማብቃት እንዳለባት ተናግረዋል፡፡
ማንም ሰው ለመታረቅ ከመጣ በእኛ በኩል ዝግጁ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመታረቅ ብቻ ሳይሆን አብሮ ለመስራትም ጭምር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሰላማዊ ትግል ለማድረግ በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡
የተገደበ ፓርቲ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደምሳሌም በኢህአዴግ ዘመን ደርግ ወይም ኢሰፓ ሆኖ በሰላማዊ መንገድ መታገል አይቻልም ነበር ሲሉ አንስተዋል፡፡
ኢህአፓም ፓርቲ ሆኖ ወደ ስራ የገባው እሳቸው በሚመሩት መንግስት ዘመን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት ገንጣይ አስገንጣይ እና ነጻ አዋጪ የሚባል ስብስብ ፓርቲ ለመባል የመጀመሪያ አድርጎ በፕሮግራሙ የሚጽፈው የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ መሆኑን እቀበላለሁ የሚለው ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፡፡
የኦነግም የህውሃትም ሆነ የሌሎች ስብስቦች የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው ካላሉ የታገሉ አይመስላቸውም፤ የዛሬዎቹም የባህር በር ጉዳይ እኛን አይመለከትም ካላሉ በስተቀር የታገሉ አይመስላቸውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እንደ አባይ ሺህ ዓመት ሸለቆ ውስጥ ሲጓዝ ይኖራል እንጂ በሃይል ስልጣን መያዝ ከዚህ በኋላ አይቻልም ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በተመለከተም ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም አንደኛ ሕውሃት ያደረገው ምርጫ ህጋዊ አይደለም እሱን ይሰርዝ ነው የሚለው ስምምነቱ፤ እሱንም ተቀብሎ እሺ ሰርዛለሁ ብሏል፡፡
ሁለተኛ፤ በምርጫው ሳቢያ የተቋቋመው መንግስት ህጋዊ ስላልሆነ ይፍረስ ነው የሚለው እሱንም እሺ ብሎ ፈርሟል፡፡
ሶስተኛ፤ ከሁሉ የተወጣጣ መንግስት ይመረጥ እሱንም እሺ፣ ቀጥሎ ደግሞ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እና ህገ መንግስትን አከብራለሁ፡፡
የፌዴራላ ጠቅላይ ሚኒስትር በህዝብ ስለተመረጥ ይቀጥላል፤ የክልሉ ፕሬዝዳንት ግን ይወርዳል ነው ስምምነቱ የሚለው እሱንም ሕውሃት ተቀብሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የታጠቀ ደግሞ ትጥቁን ፈትቶ ወደ ማህበረሰቡ ይቀላቀላል እንጂ መሳሪያ መደበቅ፣ ወታደርን ማሰልጠን ማስመረቅን አልተስማማንም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፡፡
የተፈናቀሉትም ደግሞ ወደ ቀድሞ ቄያቸው እንዲመለሱ ነው ስምምነቱ የሚያዘው የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ የተመለከቱ ጉዳዮችን ደግሞ የፌዴራል ስልጣን እንደሆነ የራሳቸው የህውሓት ህገ መንግስት ይላል፤ ይህን አልቀየርነውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነሱ ስልጣን ላይ እያሉ የሚሰራ፤ ህገ መንግስት ሲወርዱ ደግሞ የማይሰራ መሆን የለበትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል የሚካሄድ ጦርነት አይፈልግም ምክንያቱም ዓላማ እና ጥቅም ስለሌለው ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments