top of page

ጥቅምት 13 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 3 minutes ago
  • 2 min read

በሱዳን የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ከአገሪቱ ኤርፖርቶች የሚነሱ እና በኤርፖቶቹ የሚያርፉ አውሮፕላኖችን በሙሉ አወድማለሁ ሲል ዛተ፡፡


ዛቻውን ያሰሙ የፈጥኖ ደራሹ ሀይሉ አዛዥ ሌተና ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እንደሆኑ ሱዳንስ ፖስት ፅፏል፡፡


ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ትናንት ወደ አገልግሎት ተመልሷል በተባለው የካርቱም ኤርፖርት ላይ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት ሰንዝሯል ተብሏል፡፡

ree

የካርቱም ኤርፖርት ትናንት ከ2 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የሀገር ውስጥ በረራ አውሮፕላን ማስተናገዱ ታውቋል፡፡


ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ከሱዳን መንግስት ጦር ጋር ሲዋጋ ከ2 ዓመታት ከመንፈቅ በላይ ሆኖታል፡፡


ጦርነቱን ማቆሚያ አንዳችም ፍንጭ አይታይም፡፡



በአሜሪካ በሁለት የሩሲያ ታላላቅ የነዳጅ ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ ጣለች፡፡


ማዕቀቡ የተጣለባቸው ሮስ ኔፍት እና ሉክ ኦይል የተሰኙ የሩሲያ የነዳጅ ኩባንያዎች እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


አሜሪካ በሩሲያ የነዳጅ ኩባንያዎች ላይ አዲሱን ማዕቀብ የጣለችው የዩክሬይኑን ጦርነት ለማስቆም ግፊቷን ለማበርታት ነው ተብሏል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር እጅግ በጣም ጥሩ ንግግር ብናደርግም አንዳች ውጤት አላስገኙም በማለት ተናግረዋል፡፡


ትራምፕ በቅርቡ ከፑቲን ጋር በሐንጋሪ ቡዳፔስት የገፅ ለገፅ ንግግር ለማድረግ ወጥነው የነበረ ቢሆንም የቡዳፔስቱን ንግግር በይደር መተዋቸው ተሰምቷል፡፡


ሩሲያ አሁን በደረሰችበት ቦታ ጦርነቱን እንድታቆም ትራምፕ ቀደም ሲል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡


ጦርነቱን ባለበት የማቆሙ ሀሳብ በሩሲያ በኩል ተቀባይት እንዳላገኘ መረጃው አስታውሷል፡፡


አሜሪካ በሩሲያ ላይ አዲስ ማእቀብ መጣሏን ብሪታንያ ሳታረፍድ እጅግ መልካም እርምጃ ማለቷ ተጠቅሷል፡፡



እስራኤል የፍልስጤማውያን ይዞታ የሆነውን ዌስት ባንክን የሉአላዊ ግዛቷ አካል ልታደርገው ነው ተባለ፡፡


ዌስት ባንክን በተመለከተ ክኔሴት ለተሰኘው የእስራኤል ፓርላማ የተለያዩ የህግ ረቂቆች ቀርበው እየተመከረባቸው እንደሆነ JNS ፅፏል፡፡


ዌስት ባንክን ወደ እስራኤል ማጠቃለል ያስችላል የተባሉ የህግ ረቂቆች ለፓርላማው የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ቋሚ ኮሚቴዎች መመራታቸው ታውቋል፡፡


በአለም አቀፍ ህግ ዌስት ባንክ የፍልስጤማውያን ይዞታ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡


ዌስት ባንክ የፍልስጤማውያን ይዞታ ቢሆንም በስፍራው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ሰፍረውበት ይገኛሉ፡፡


የፍልስጤም አስተዳደር ዋና መቀመጫው በዌስት ባንክ ራማላህ ቢሆንም ሙሉ የፀጥታ ቁጥጥሩ በእስራኤል እጅ መሆኑ ይነገራል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page