ጥቅምት 12 2018 ለሰላም፣ ለእድገት ሲባል መንግስት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ፖለቲከኞች እና ነፍጥ ያነሱ ታጣቂዎች ወደ መግባባት እንዲመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ፡፡
- sheger1021fm
- 18 minutes ago
- 1 min read

ፓርትርያርኩ ይህንን የሰላም ጥሪ ያቀረቡት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በተጀመረበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡
በሀገሪቱ ያለው አለመረጋጋት በህዝብ አጠቃላይ ስነ ልቦና፣ በሀገሪቱ አንድነትና እድገት ላይ የሚያስከትለው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ያሉት አባ ማቲያስ ፣ የህዝቡ ስነ ልቦና ከተጎዳ የነገው እድል ጤናማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም ብለዋል፡፡
ችግሩ እየታየ ያለው በዋናነት በሀገራችን ፖለቲከኞች በመሆኑ ነገሩ የተወሳሰበና የተራዘመ እንዲሆን አድርጎታል ሲልም አክለዋል፡፡
በመሆኑም ይህ የርስ በርስ ግጭት ቆሞ ችግሮች በውይይትና በድርድር በመፍታት የወንድማማች እልቂት የሚያስቆም የሰላምና የዕርቅ ዕድል ቅድሚያ እንዲሰጠው ጉባኤው የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይገባዋል ሲል አባ ማቲያስ ጠይቀዋል፡፡
የነገው ትውልድ ልማታዊ ተስፋ እውን ሊሆን የሚችለው ሰላምና አንድነት ሲኖር ያሉት ፓትርያርኩ መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችና ነፍጥ ያነሡ ወገኖች ሁሉ ለሰላም መስፈንና ለልማት ዕድገት መረጋገጥ ሲባል ወደ መግባባት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጎደሉባቸው ነገሮች ብዙ ናቸው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ያሉትን ከፍተቶች ለማረም ፈጣን ፣ ቁርጥና አዋጭ የሆነ ስራ ካልተሰራ ለወደፊት የቤተ ክርስቲያን ህልውና ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኗን በአደባባይ እየተዳፈሩ ያሉትንም በህግ አግባብ ነገሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s