top of page

ጥቅምት 1፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች



የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ከተቃዋሚው ብሔራዊ የአንድነት ፓርቲ መሪ ቤኒ ጋንቴዝ ጋር የጦር ወቅት ጊዜያዊ መንግስት ለመመስረት ተስማሙ፡፡


የአገሪቱ ጦር መሰረቱን በጋዛ ሰርፅ ካደረገው የፍልስጤማውያ የጦር ድርጅት ሐማስ ጋር ውጊያ ከገጠመ ዛሬ 6ኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡


ሐማስ ባለፈው ቅዳሜ ወደ እስራኤል ይዞታዎች በመዝለቅ ድንገት ደራሽ ጥቃት በማድረሱ በእስራኤላውያን ዘንድ ቁጣ እና ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡


ኔታንያሁ እና ጋንቴዝ ጊዜያዊውን የጦር ወቅት ካቢኔ ለማቋቋም የተስማሙት የፖለቲካ ተቃርኗቸውን ወደ ጎን በማለት በጋራ ለመቆም እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የዋነኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር መሪ ያኢር ላፒድ ግን አዲሱን ጥምረት እንዳልተቀላቀሉ ተሰምቷል፡፡


አዲሱ ካቢኔ ጦርነቱ ዳር እስኪደርስ እንደሚዘልቅ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


ኔታንያሁ የሐማስ አባላትን ለወሬ ነጋሪ ሳናስቀር በሙሉ እንጨርሳቸዋለን ማለታቸውንም ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የተቃዋሚው መሪ ቤኒ ጋንቴዝም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ንግግር ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡


ጋንቴዝም ሐማስን ከእንግዲህ ከምድረ ገፅ እናጠፋዋለን ብለዋል፡፡


አዲሱ ካቢኔ የጦር አመራር ውሳኔዎችን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡


የፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት ሐማስ በእስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ ድንገት ደራሽ ጥቃት ማድረሱ እስራኤልን ክፉኛ ማስቆጣቱ ይነገራል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን እስራኤል ራሷን የመከላከል መብቷ የተጠበቀ ቢሆንም እርምጃዋ በአለም አቀፍ የጦርነት ህግ ሊመራ ይገባዋል ማለታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡



የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ ፍልስጤማውያኑ ጋዛ ሰርፅ እንደ ምግብ ፣ ውሃ እና ነዳጅ ያሉ ለእለት ከእለት ሕይወት አስፈላጊ ነገሮች ሊገቡ ይገባል አሉ፡፡


ጉቴሬዝ ለሰብአዊ አቅርቦትም መንገዶች እንዲከፈቱ መጠየቃቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


እስራኤል ምግብ ፣ ውሃ እና ነዳጅ ወደ ጋዛ ሰርፅ እንዳያልፍ መከልከሏን ዘገባው አስታውሷል፡፡


ወደ ጋዛ የሚያልፈውንም ኤሌክትሪክ አቋርጣለች፡፡


የእስራኤል እርምጃ ለወትሮውም ሰብአዊ ቀውስ ተለይቶት በማያውቀው ጋዛ ሰርፅ ችግሩን ይበልጥ እንደሚያባብሰው ተሰግቷል፡፡


በዚህም የተነሳ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰብአዊ አቅርቦቱ ግዴታ ሊፈቀድ ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



የኒጀር ወታደራዊ መንግስት በአገሪቱ የተባበሩት መንግስታት የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ መሪ ለቀው እንዲወጡ ጠየቁ፡፡


የልዑክ ቡድን መሪው ኒጀርን ለቅቀው እንዲወጡ ከትናንት አንስቶ የ72 ሰዓታት ጊዜ እንደተሰጣቸው አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


የመንግስታቱ ድርጅት የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ መሪ ኒጀርን ለቅቀው እንዲወጡ የታዘዙት በቅርቡ በተካሄደው 78ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተገቢው ሁኔታ እንዳንካፈል መሰናክል ፈጥረዋል ተብለው ነው፡፡


የኒጀር የጦር አለቆች ከ2 ወራት በፊት ቀድሞውን ፕሬዘዳንት ሞሐመድ ባዙምን መንግስት በመገልበጥ ስልጣን መያዛቸው ይታወቃል፡፡


በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተሳትፏቸው የተስተጓጎለው በዚሁ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

bottom of page