ጥር 19/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 16 hours ago
- 2 min read
ፈረንሳይ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊዎችን የኢንተርኔት ማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚነትን ልታስቀር ነው፡፡
አዳጊዎችን እንደ ፌስ ቡክ እና ቲክ ቶክ ካሉ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ተጠቃሚነት የሚከለክል ረቂቅ ተሰናድቶ ለአገሩቱ ፓርላማ መቅረቡን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሕጉ ከመጪው አዲስ የትምህርት ዘመን በፊት ስራ ላይ እንዲውል ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሕጉ አዳጊ ወጣቶችን ከተለያዩ ማህበራዊ ጠንቆች ለመጠበቅ ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆን ታምኖበታል ተብሏል፡፡
በብዙ አገሮችም አዳጊዎችን ከተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች የማቅረቡ እርምጃ እያነጋገረ ነው ተብሏል፡፡
አውስትራሊያ እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊዎችን የማህበራዊ ትስስር ገፆች ተጠቃሚነት በመከልከል ቀዳሚዋ አገር እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
በስፔን የፈጣን የመጓጓዣ ባቡሮች ፍጥነት እንዲቀንስ ተደረገ፡፡
በስፔን የፈጣን ባቡሮች ፍጥነት እንዲቀንስ የተደረገው በአገሪቱ ሁለት አደጋዎች መድረሳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
በአገሪቱ እጅግ ፈጣኖቹ ባቡሮች በሰዓት እስከ 300 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት ሲከንፉ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በአሁኑ የጥንቃቄ እርምጃ ግን የባቡሮቹ ፍጥነት በሰዓት ወደ 80 ኪሎ ሜትር እንዲቀንስ መደረጉ ታውቋል፡፡
በስፔን ደቡባዊ ክፍል በደረሰው ግጭት የ45 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡
በስፔን ከአደጋዎቹ በኋላ ቀደም ብሎ የባቡሮቹ ፍጥነት በሰዓት 230 ኪሎ ሜትር እንዲሆን ተደርጎ ነበር ተብሏል፡፡
በናይጀሪያ የፕሬዘዳንት ቦላ ቲኑቡን መንግስት ለመገልበጥ አሲረው ነበር የተባሉ 16 የጦር መኮንኖች ከወታደራዊ ችሎት ፊት ሊቀርቡ ነው ተባለ፡፡
ግለሰቦቹ በደፈናው በወታደራዊ ሥርዓት ማጓደል በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ጥቅምት ወር እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ይሁንና አሁን ጦር ፍርድ ቤት ይቀርባሉ የተባሉት 16 የጦር መኮንኖች በተያዙ ጊዜ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጉምጉምታ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
ግለሰቦቹ ጉዳያቸው ሲታይ ሚዛናዊ ፍትህ እንደሚያገኙ የጦር ሹሞች ተናግረዋል፡፡
ናይጀሪያ በታሪኳ በርካታ ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣዎችን ያሳለፈች አገር እንደሆነች በመረጃው ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡
አገሪቱ ከወታደራዊ አስተዳደር ከተገላገለች 27 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም ቀጣዩ ምዕራፍ ቀዳሚ ተግባር የሰርጡ መልሶ ግንባታ ሳይሆን ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት ይሆናል አሉ፡፡
ኔታንያሁ የጋዛን ቀጣይ የተኩስ አቁም ምዕራፍ በተመለከተ የተናገሩት ክኔሴት ለተሰኘው የአገራቸው ፓርላማ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በጋዛ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ባቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች የሰላም እቅድ የተኩስ አቁም ከተደረሰ ከ2 ወራት በላይ ሆኖታል፡፡
የተኩስ አቁም ተደርሷል ቢባልም እስራኤል በመረጠችው ጊዜ እና ቦታ በጋዛ ድብደባ ስትፈፅም ቆይታለች፡፡
ትራምፕ ለጋዛ ቀጣይ የሰላም ምዕራፍ በቅርቡ በስዊዘርላንድ ዳቮስ አለም አቀፉን የጋዛ ሰርጥ ቦርድ ማብሰራቸው ይታወቃል፡፡
ይሁንና የቦርዱ ሚና እና የተልዕኮ አድማስ በከፍተኛ ደረጃ እያነጋገረ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ












Comments