በጋሞ ዞን ሰሞኑን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር 64 መድረሱ ተነገረ።
- 1 hour ago
- 1 min read
መጋቢት 3/2018
በጋሞ ዞን ሰሞኑን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር 64 መድረሱ ተነገረ።
የተጎዱትን በህይወት የማትረፉ ስራ ከዚህ በውሃላ ብዙም ተስፋ የለውም፣ቀሪ የአስከሬን ፍለጋ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ተብሏል።
የሟቾቹ ቁጥር 52 ስለመድረሱ አስቀድመን ነግረናችሁ የነበረ ሲሆን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የተጨማሪ ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ተናግሯል።
እስካሁን አስከሬናቸው የተገኘ የሟቾች ቁጥርም 64 ደርሷል ብሏል።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ በአካባቢው ነዋሪ የነበሩና በአደጋው የጠፉ ሰዎች ቁጥር 128 መሆኑን ተናግሯል።

እስካሁን ባለው መረጃ ከዚህ ውስጥ የ64ቱ ሰዎች አስክሬን መገኘቱን የጋሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አብረሀም ቡሔ ተናግረዋል።
ኢንስፔክተሩ በሶስት ወረዳዎች አደጋ ተመዝጋቧል ያሉ ሲሆን ከሁሉም ከባድ አደጋ ያስተናገደው ዳጮ ባባ የተባለው ወረዳ ነው ብለዋል።
ከዚሁ ወረዳ ብቻ የ59 ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ገልጸው የሌሎች አምስት ሰዎች አስከሬን ደግሞ በቦንኬና ከምባ ዙሪያ ወረዳ መገኘቱ ተነግሯል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ የተለያየ መረጃ እየቀረበ ሲሆን ይህም የተሳሳተና የተዛባ መረጃ ነው ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በህይወት የማግኘቱ ተስፋም እየተመናመነ መጥቷል ተብሏል።
ከዚህ በኋላ ቀሪ የጠፉ ሰዎችን አስክሬን ፍለጋ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ተናግሯል።

