top of page

ግንቦት 13 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 7 hours ago
  • 2 min read

ብሪታንያ ከእስራኤል ጋር ጀምራ የነበረውን የነፃ ንግድ ንግግር አቋረጠች ተባለ፡፡


የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር ስታርመር መንግስት ከእስራኤል ጋር ሲደረግ የነበረውን ንግድ ነክ ንግግር ያቋረጠው እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ባከፋችው የጦር ዘመቻ ምክንያት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የብሪታንያ መንግስት በጋዛ የእስራኤል የከፋ የጦር ዘመቻ ከትዕግስቴ በላይ ሆኖብኛል ማለቱ ተሰምቷል፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሐማስ ታጋቾችን ከለቀቀ እና ትጥቅ ከፈታ ጦርነቱ ወዲያውኑ ይቆማል የሚል መሟገቻ አቅርበዋል፡፡


በእስራኤል የጋዛ ዘመቻ የተገደሉት ፍልስጤማውያን ብዛት ከ53 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡


አብዛኞቹም የጦርነቱ ሰለባዎች ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡



በአሜሪካ ብሬይን መርፊ የተባሉ ዳኛ የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የችሎት መድፈር እየፈፀመ ነው ሲሉ አማረሩ፡፡


አስተዳደሩ አስሯቸው የነበሩ ጥገኝነት ፈላጊዎችን ወደ ደቡብ ሱዳን መላኩ በጭራሽ ያልተገባ ተግባር እንደሆነ ዳኛው መናገራቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ወደ ደቡብ ሱዳን ከተላኩት ከአሜሪካ ተባራሪ ጥገኝነት ፈላጊዎች መካከል እስያውያን ጭምር አሉበት ተብሏል፡፡


ዳኛው ቀደም ሲል ስደተኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን ሳያስረዱ በጭራሽ ወደ 3ኛ አገር እንዳይላኩ አዝዘው እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ሀላፊነት ከመጣ ወዲህ ሰነድ አልባ ናቸው የተባሉ ስደተኞችን እያፈሰ በማሰር ከአገር ማባረሩን ገፍቶበታል፡፡


ሒደቱም ውጥንቅጥ የበዛው መሆኑ ይነገራል፡፡



የሱዳን ወታደራዊ መንግስት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በቀጥታ በሰው አልባ በራሪ አካላት /ድሮኖች/ ጥቃት እያደረሰችብን ነው የሚል ክስ አሰማ፡፡


የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ክሱን ያሰማው በተባበሩት መንግስታት ልዩ ወኪሉ አማካይነት እንደሆነ ሱዳንስ ፖስት ፅፏል፡፡


ልዩ ወኪሉ አል ሐርቲ ኢድሪስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በወደብ ከተማዋ ፖርት ሱዳን ላይ በተከታታይ የተፈፀመው የድሮን ጥቃት በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


ኢሚሬትስ በፖርት ሱዳን ላይ ተከታታይ የድሮን ጥቃቱን የፈፀመችው በቀጠናው ያሉ ጦር ሰፈሮቿን እና የጦር መርከቦቿን በመጠቀም እንደሆነ አስተማማኝ የደህንነት ማስረጃ አግኝተናል ብለዋል ልዩ ወኪሉ፡፡


የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በማስታጠቅ ስሟ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል፡፡



በአንጎላ አንድ የነዳጅ ማምረቻ ስፍራ በደረሰ የቃጠሎ አደጋ በ11 ሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት ደረሰባቸው ተባለ፡፡


የቃጠሎ አደጋው የደረሰው በባህር ዳርቻ በሚገኝ የነዳጅ ማምረቻ ስፍራ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡


በቃጠሎው አደጋ ከደረሰባቸው መካከል አራቱ ለሕይወታቸው ያሰጋቸዋል ተብሏል፡፡


ሁሉም የአደጋው ተጎጂዎች በሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡


በነዳጅ ማምረቻው ስፍራ በምን ምክንያት ቃጠሎው እንደተቀሰቀሰ የተነገረ የለም፡፡


የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው ተብሏል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page