የፎርዋርድ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ያለ ብሔራዊ ባንክ ማረጋገጫ ማካሄድ እንዲችሉ መፍቀዱ ነው፡፡
- 56 minutes ago
- 2 min read
የካቲት 9/2018
በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ መመሪያ ላይ በ19 ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎች ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የፎርዋርድ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ያለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማረጋገጫ ማካሄድ እንዲችሉ መፍቀዱ ነው፡፡
ይህ ማለት አንድ ነጋዴ አንድ ሺህ ዶላር የሚያወጣ ሰሊጥ ወደ አረብ ሀገር ቢልክ ከባንኮች ጋር የላከው ሰሊጥ ገበያ ላይ ተሽጦ የሚመጣው የውጪ ምንዛሪ ከወዲሁ ባንኩ የሚገዛበትን ዋጋ መዋዋል ይችላል፡፡
ይህ ሲያደርግ ውል የተስማሙበት ጊዜ እና ሰሊጡ የተሸጠበት ወቅት ያለው የውጪ ምንዛሪ ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት የሚፈጥረውን ስጋት ከወዲሁ ለማስቀረት ይረዳል ተብሏል፡፡
አቶ ጥላሁን ግርማ የፋይናንስ ኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት አማካሪ ናቸው፡፡ የፎርዋርድ የውጪ ምንዛሪ ግብይት በፅሁፍ የተፈቀደ ነገር እስካሁን አልተመለከትሁም ይላሉ፡፡

መመርያው ሲተገበር አስመጪዎችና ላኪዎች በመግዣ ገንዘብ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለው የመጨመርና ዝቅ የማለት ስጋት ለመቀነስና ኪሳራን ለመከላከል ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ይህ ባለመተግበሩ አስመጪዎችና ላኪዎች የመገበያያ ገንዘብ በመቀነሱ ምክንያት ለኪሳራ ሲዳረጉ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
በተለይም የደላር ምንዛሪ በገበያ ይወሰን በተባለበት ወቅት ድንገት የብር የመግዛት አቅም መዳከሙን ተከትሎ ብዙ አስመጪዎችና ላኪዎች ኪሳራ ገጥሟቸው ነበር ሲሉም ያስታውሳሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በውጪ ሀገር መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሲፈልጉ ሀገሪቱ ትከተል የነበረው አሰራር አመቺ አልነበረም ይላሉ፡፡
እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የውጪ ባለሃብቶችን ስትስብ ነበር ያሉት አቶ ጥላሁን ግርማ ብሄራዊ ባንክ ያሻሻለው አዲሱ መመርያ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በውጪ ሀገር መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት ጉዳይ አገልግሎት በመስጠት የውጪ ምንዛሪ የሚያመጡ ተቋማት የበለጠ እንዲሰሩ የሚያደርግ ተካቷል፡፡
የአገልግሎት ላኪዎች ከወጪ ንግድ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ሙሉ በሙሉ በሪቴንሽን ሂሳባቸው ያለ ምንም የጊዜ ገደብ እንዲይዙ ተፈቅዷል የሚለው ማሻሻያ ለእነዚህ ተቋማት ይበልጡን ጠቃሚ ነው ሲሉም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ጥላሁን ግርማ ያስረዳሉ፡፡
ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸው አንዳንድ ማሻሻያዎች ለረጅም ጊዜ የሚጠየቁ ጉዳዮች ነበር የሚሉት ባለሙያው ማስፈፀሙ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7








