የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት እና የአደጋ ጊዜ ፈንድ ማቋቋሚያ ደንብ
- 3 hours ago
- 2 min read
የካቲት 9/2018
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት እና የአደጋ ጊዜ ፈንድ ማቋቋሚያ ደንብ የመንግስት ሰራተኛው እና ተሿሚዎች ከወር ደመወዛቸው 0.5 በመቶ እንዲቆረጥባቸው ያስገድዳል፡፡
የሚሰበሰበው ገንዘብ በከተማዋ ለሚያጋጥሙ የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚውል መሆኑ ተነግሯል፡፡
ደንቡ ከሃይማኖት ተቋማት በየዓመቱ ከእያንዳንዱ አጥቢያ 12 ሺህ ብር ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፍቃድ ሲያወጡ እና ሲያድሱ በዓመት 5 ሺህ ብር፣ የከተማዋ ነዋሪ ከውሃ ክፍያ ጋር የሚታሰብ በወር 5 ብር ተደምሮ እንዲከፍል ያዛል፡፡
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የመጠባበቂያ ዕቅድ መነሻ በድህረ አደጋ ወቅት ከአደጋ ጉዳት ለማገገም፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ፣ ለመልሶ ግንባታና በዘሊቂነት ማቋቋም እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ ዝግጁነትና የአደጋ መቋቋም አቅምን ማረጋገጥ ከፈንዱ አላማዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው ፡፡
በየዓመቱ ከከተማው አስተዲደር የሚመደብ ተዘዋዋሪ የአደጋ ዝግጁነት መጠባበቂያ በጀት፤ ከአጋር አካላት፣ከሀገር ውስጥና ውጭ ከሚገኙ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና በጎ አድራጎት ተቋማት እና ሌሎች የፈንዱ ምንጮች መሆናቸው በደንቡ ተመላክቷል፡፡
ደንቡ ሰለ ፈንዱ ገቢ አሰባሰብ ሲዘረዝር ከከተማዋ ባለ በጀት መስሪያ ቤት ሥራ ማስኬጃ በጀት 1 በመቶ፣ከመንግስት ሰራተኛው እና ተሿሚዎች ከወር ደሞዛቸው 0.5 በመቶ፣ከከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ልማት ድርጅት የሥራ ማስኪያጃ በጀት 2 በመቶ እንዲሰበሰብ ይላል ፡፡
በተጨማሪም ከንግዱ ማህበረሰብ ከደረጃ "ሀ" ግብር ከፋይ በወር 200ብር ፣ከደረጃ "ለ"በወር 100 ብር እንዲሁም ከ "ሐ" በወር 50 ብር በግብር አሰባሰብ ወቅት ከግብር ጋር ተሰልቶ እንዲከፍል ደንግጓል፡፡
ከቋሚ ንብረት ሽያጭ እና ግዢ 0.1 በመቶ ይሰበሰባልም ይላል።
በዚህም መሰረት የከተማዋ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ከመንግስት ሰራተኛው እና ተሿሚዎች ከወር ደሞዛቸው 0.5 በመቶ እንዲቆረጥ የሚያዘው ደንጋጌ ከጥር 01 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ለሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች የጻፈው ደብዳቤ ያሳያል፡፡
ደንቡ ጸድቆ ተግባራዊ እንዲሆን የተደነገገው ከመጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ቢሆንም እስካሁን ተፈጻሚ መሆን የቻለው ከመንግስት ሰራተኞች እንዲቆረጥ የሚያዘው ክፍል ብቻ ነው፡፡
እሱም ተግባራዊ መሆን የጀመረው ካለፈው ጥር 01 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
የኢትዮጵያ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ ከሰራተኛው ወርሃዊ ደሞዝ እንዲቆረጥ የሚያዘውን ድንጋጌ ማስቀረቱ ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን ከመንግስት ሰራተኞች 0.5 በመቶ እንዲቆረጥ ወስኗል።
ባንኮች ከሚሰጡት አገልግሎት ፣ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ፣ከኢንሹራንሶች ፣ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሸጠው የድምጽ እና ኢንተርኔት ጥቅል፣ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ፣ከንግድ ፍቃድ ሲወጣ እና ሲታደስ ፣ በጉሙሩክ ኮሚሽን ከሚያዘው ኮንትሮባንድ እቃ፣ከፓስፖርት እና ቪዛ አገልግሎት ክፍያ እንዲሁም ከሎሎች አገልግሎቶች ገቢው እንዲሰበሰብ መወሰኑ እና መሰብሰብ መጀመሩም ይታወቃል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7








