top of page

የካቲት 15፣2016 - በኦሮሚያ ክልል ከጥቅምት 30፣ 2016 በፊት ባሉት 2 ዓመታት ከሕግ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎች እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መሆናቸውን ኢሰመኮ ተናገረ

በኦሮሚያ ክልል ከጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት ከሕግ ወይም ከፍርድ ውጪ የሆኑ እና በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ተናገረ፡፡


ኮሚሽኑ የሁለቱን ዓመታት ግኝቶች ይፋ ያደረገው በክልሉ ቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ እና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች ላይ አተኩሮ መሆኑን ባወጣው ምግለጫ ጠቅሷል፡፡


መረጃ እና ማስረጃዎች ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂዎች ቤተሰቦች፣ ከዐይን ምስክሮች፣ ከሕክምና ባለሞያዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአባገዳዎች እና ከመንግሥት አካላት በአጠቃላይ 158 ሰዎችን በማነጋገር ያወጣው ሪፖርት መሆኑንም አስረድቷል።


በሪፖርቱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” በመባል የሚጠራው) እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ‘’ኢ- መደበኛ’’ ታጣቂዎች በንጹሃን ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች ተዳሰዋል፡፡


በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሲቪል ሰዎች ላይ ለሚደርስ የመብቶች ጥሰት እንደ ዋነኛ ምክንያት የተጠቀሰው በመንግሥት የጸጥታ አካላት በኩል “ለታጣቂ ቡድኖች መረጃ እና ሎጂስቲክስ ታቀርባላችሁ፣ የቡድኑ አባል ናችሁ’’ የሚሉ መሆንኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡


በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ’’) በኩልም “ለመንግሥት መረጃ ትሰጣላችሁ፣ የቤተሰብ አባላችሁ በመንግሥት ጸጥታ ኃይል ውስጥ እያገለገለ ነው ወይም ከእኛ ጋር በመሆን አልታገላችሁም፣ ድጋፍ አላደረጋችሁም’’ የሚል ምክንያት እንደሚቀርብ ተነስቷል፡፡


በተመሳሳይ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ‘’ኢ-መደበኛ’’ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች በጅምላ “በኦነግ ሸኔነት” በመፈረጅ እና የክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎችን በማንሳት በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ዘረፋ እና ማፈናቀል እንደሚፈጸም ኮሚሽኑ አስረድቷል።


በዚህም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎችን በመጣስ በግጭት ወይም በውጊያ ዐውድ እና ከውጊያ ዐውድ ውጭ በርካታ ሲቪል ሰዎችን ከሕግ ወይም ከፍርድ ውጪ መግደላቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ብሏል።


ኮሚሽኑ የተገደሉትን በርካታ ሰዎች ማንነታቸውን ማጣራትና ማረጋገጥ ችያለሁ ሲል ጠቅሷል፡፡

በርካታ ሲቪል ሰዎች ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት፣ ለተስፋፋ እገታ፣ መፈናቃል እና ዝርፊያ መዳረገቸውን ደርሼበታለሁ ሲልም ኮሚሽኑ ዛሬ ይፋ ባደረገው ባለ 11 ገጽ ሪፖርት አስረድቷል።


በተለይም ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች እና ሌሎች በሰዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶች “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች” ናቸው ሲል ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡


ስለሆነም ፈጣን፣ ገለልተኛ እና የተሟላ የወንጀል ምርመራ ሊደረግባቸው እና ተጠያቂነት ሊረጋገጥበትና ተጎጂዎችም ሊካሱበት ይገባል ሲል አስረድቷል፡፡


ኮሚሽኑ ክትትል እና ምርመራውን መሠረት በማድረግ ከሕግ፣ ከፍርድ ውጪ የሆኑ እና በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ መሆናቸውን አስገንዝቧል፡፡


በተለይም የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ አካላት ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት ማረጋገጥን ጨምሮ ዘላቂ መፍትሔ በአስቸኳይ እንዲሰጡ ኮሚሽኑ ጥሪ አድርጓል።


በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ የሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን፣ መርሖችንና ድንጋጌዎች እንዲያከብሩ በተለይም በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡


የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ለቀጠለው ግጭትና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሁሉም ወገኖች በቁርጠኝነት ሰላማዊ ውይይትን ከመቀበልና ከመተግበር ውጪ መፍትሔ የለም፣ የግጭቶቹ መራዘምም የሰዎችን ሥቃይ ያራዝማል እንጂ መፍትሔን አይወልድም” ብለዋል።



ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



bottom of page