የእግረ መንገድ ቱሪዝም ወይም (Stop Over Tourism)
- 21 minutes ago
- 2 min read
ሚያዝያ 6/2018
የእግረ መንገድ ቱሪዝም ወይም ( #Stop_Over_Tourism) በመባል የሚታወቀው የቱሪዝም አይነት ተጓዦች ከአንዱ ወደ ሌላው ሃገር ለመጓዝ መሸጋገሪያ በሚያደርጉት ሃገር እግረ መንገዳቸውን የሚያደርጉት ጉብኝት ነው።
ለዚህ ደግሞ በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮኖች ለአየር በረራው መሸጋገሪያ የሚያደርጓት አዲስ አበባ ተመራጭ እየሆነች ነው ተብሏል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእግረ መንገድ ቱሪዝም "የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝምን ለማሳደግ ያለመ የመግባቢያ ስምምነት ባለፈው ዓመት ነበር የተፈራረሙት።
ከዚያስ በኋላ ምን እየተሰራ ነው ያልናቸው በዚህ ስራ ውስጥ በየደረጃው ካሉ የመንግስት ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ ለተጓዦቹ ለ7 ቀናት የሚቆ ነፃ የቪዛ አገልግሎት ተጀምሯል፤ ለጉዞ የሚሆኑ የተለያዩ ፓኬጆችም ተዘጋጅተዋል ብለውናል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአየር መንገዷ በኩል የሚያልፉ ከ15 ሚሊዮን በላይ አለም አቀፍ መንገደኞች በመኖራቸው ይህንን እድል ለመጠቀም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ የእግረ መንገድ ቱሪዝም ትኩረት ተሰጥቶት፤ ስትራቴጂም ተቀርፆለት እየተሰራበት ይገኛል ተብሏል።
ይሁንና ከእነዚህ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ መንገደኞች እስካሁን በዚህ የእግረ መንገድ ቱሪዝም የምን ያህሉን የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም ተችሏል? ተብሎ ከተጠየቀ እንደ ሃገር የቱሪዝም ሃብት አንፃር በጣም ጥቂቱ ናቸው የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያራዝሙት።
በኢትዮጵያ አዲስ በፀደቀው የ"ስቶፕ ኦቨር" (Stopover) ቱሪዝም ፖሊሲ መሰረት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚጓዙ የትራንዚት መንገደኞች ከ24 ሰዓት እስከ 7 ቀናት ለሚደርስ ቆይታ ያለ ቪዛ ክፍያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው መጎብኘት እንደሚችል ተቀምጧል።
ለመሆኑ አዲስ አበባ የእግረ መንገድ ጎብኚዎቿ በአገልግሎቷ ተደስተው፤ ምርጫቸውን፤ ውሎ አዳራቸውን በከተማዋ እንዲያደርጉ፤ ይዘው የመጡትን እዚሁ እንዲያወጡ ለማድረግ ምን ያህል ዝግጁ ናት? ያልናቸው ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በአዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ ዘመናዊ መንገዶች፣መዝናኛ ቦታዎችና ሌላውም ጎብኚዎችን ለመሳብ ነው ውጤቱን ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያየነው ነው ብለውናል፡፡
በቱሪዝሙ ዘርፍ የተሰማሩ አስጎብኚ ድርጅቶችስ የእግረ መንገድ ቱሪዝምን ጨምሮ በሌላ ሌላውም ምን አገዛችሁ?ስንል ጠይቀናል፡፡
የጳጉሜን አስጎብኚና የጉዞ ወኪል አክሲዮን ማህበር የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ እዮብ አባተ በርከት ያሉ ጎብኚዎችን የሚስተናግዱ ዘመናዊ ባሶችን በማቅረብ የተመቸ አገልግሎት እየሰጠን ነው ብለውናል፡፡
በሌላ በኩል አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን አጥንቶ ፓኬጆችን በማዘጋጀት ለመስራት ቢሞከርም በሃገሪቱ ያለው የፀጥታ ችግር አላሰራ ብሎናል ባይ ናቸው፡፡
ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የውጭ ሃገር ጎብኚዎችን ለመሳብ አገልግሎታቸውን ቀልጣፋ እያደረጉ መሆኑን የነገሩን የቀርሚሎች አስጎብኚ ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አመለወርቅ ብርሃኑ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የክልል ከተሞች ተንቀሳቅሶ ማስጎብኘት አደጋ ስላለው ወደ ክልሎች አንወጣም ብለውናል፡፡
ከተለያዩ ሃገራት የሚመጡ ቱሪስቶች አማካይ የቀን ወጪያቸው 234ዶላር ወይም በወቅቱ ምንዛሬ ሲሰላ 34ሺህ 500 ብር ይደርሳል።
በአብዛኛው የውጭ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ እስከ 16 ቀን የሚዘልቅ ነው።
አዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት ከ700 ሺህ የውጭ ሃገር ጎብኚዎች 155 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘች የከተማ አስተዳደሩ ማሳወቁ ይታወሳል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…..
ምንታምር ፀጋው

