top of page

የኢኮኖሚ ድርጅቶችን እንዲቆጥሩ 40,000 ወጣቶች ተሰማርተዋል ተባለ፡፡

  • sheger1021fm
  • 3 hours ago
  • 2 min read

ህዳር 2 2018

 

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢኮኖሚ ድርጅቶችን እንዲቆጥሩ 40,000 ወጣቶች ተሰማርተዋል ተባለ፡፡

 

ይህንን ያለው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ነው፡፡

 

አገልግሎቱ ድርጅቶቹን እንዲቆጥሩልኝ ያሰማራኋቸው ወጣቶች ሁሉም የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው ብሏል፡፡

 

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ከጥቅምት 1 ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 2018 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም አይነት የኢኮኖሚ ድርጅቶች መረጃ የመቁጠር ስራ እየከወነ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

 

በዚህ ቆጠራ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢኮኖሚ ድርጅቶ ብዛት፣ በምን ዘርፍ እንደተሰማሩ፣ ያላቸው የሰው ሀይል፣ የሚገኙበት ቦታ፣ የሚጠቀሙት የግብዓት ዓይነት መጠንና ምንጭ፣ የምርት ሽያጮቻቸውና ምን ያህል ኤክስፖርት እንደሚያደርጉ እንዲሁም በስራቸው የሚገጥሟቸው ችግሮች  ይመዘገባል ተብሏል፡፡

 

ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከወነ ነው ለተባለው ለዚህ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራም 40,000 ወጣቶች ስልጠና ተሰጥቷቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰማራታቸውን ተነግሯል፡፡

 

ይህንን የነገሩን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የህዝብ ግኑኝነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ሳፊ ገመዲ ናቸው፡፡

 

ree

ለመሆኑ ይህ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ጠቀሜታው ምንድነው ብለን የጠየቅናቸው ሀላፊው፣ ለፖሊሲ ግብዓት፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለተያያዥ ዘርፎች የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል አስረድተዋል፡፡

 

አንዳንድ የንግድ ተቋማት በመንግስት በኩል እንዲህ አይነት መረጃዎች ሲጠየቁ ያለቸው ንብረት፣ የሰው ሀብት ብዛት በትክክል ያለማሳወቅ ወይም ካላቸው ላይ ቀንሰው ሲናገሩ እንደሚስተዋልም ይነገራል፡፡ ለዚህም መንግስት ግብር ሊጨምርብን ነው በሚል ስጋት እንደምክንያት ሲጠቀሱ ይሰማል፡፡

 

ታዲያ ይህ ለማድ በቆጠራው ላይም ሆነ ትክክለኛ መረጃ በማሰባሰብ ሂደቱ ተፅዕኖ አይኖረውም ወይ ያልናቸው ሀላፊው፣ በቆጠራው የሚገኘው መረጃ ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ ለመረጃ ምንጭነት ብቻ የሚያገልግልና ከግብርም ሆነ ከሌሎች ክፍያዎች ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም ብለውናል፡፡

 

የድርጅቱን መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን የተገኘ ተቋም የተገኘ እንደሆነ መረጃ እንዲሰጥ የሚያስገድድው የህግ ማዕቀፍ ስለመኖሩም የጠየቅናቸው አቶ ሳፊ ገመዲ፤ መረጃ እንዲሰጡ የሚደነግግ ህግ መኖሩን ጠቅሰው በጉዳዩ ላይ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በሰፊው እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

 

ከተጀመረ 1 ወር ባስቆጠረው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ፤ በከተማውም ሆነ በገጠሪቱ የሀገሩ ክፍሎች የሚገኙ፣ የማምረቻ፣ የንግድ፣ የግንባታ፣ የማዕድንና የአገልግሎት ዘርፎች በአጠቃላይ ለገበያ ሚቀርቡ ሁሉም አይነት ምርቶችና አገልግሎቶች እንደሚቆጠሩ ተነግሯል፡፡

 

ማንያዘዋል ጌታሁን

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page