የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት 3 ወራት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተከትሎ በተቋሙ ተልዕኮ ላይ ከፓርላማ ጥያቄ ቀረበበት።
- sheger1021fm
- 40 minutes ago
- 2 min read
ህዳር 8 2018
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት 3 ወራት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተከትሎ በተቋሙ ተልዕኮ ላይ ከፓርላማ ጥያቄ ቀረበበት።
በተቋሙ ላይ ጥያቄ የተነሳበት አገልግሎቱ የ3 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርቱን በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ከሰዓት በፊት ባቀረበበት ወቅት ነው።
የተቋሙን የ3 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባለፉት 3 ወራት ከ545,000 በላይ የሚሆኑ ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት አግኝተዋል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ ለ373,000 በላይ ዜጎች መደበኛ፣ ከ136 በላይ ለሚሆኑት አስቸኳይ ፣ ከ14,000 በላይ ኢ-ፓስፖርት እንዲሁም ከ20,000 በላይ ለሚሆኑት ደግሞ በቆንጽላ በኩል በአጠቃላይ ከ545 ሺ በላይ ዜጎች አገልግሎት ተሰጥቷል ሲሉ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

በሩብ ዓመቱ ለመስጠት ታስቦ የነበረው ፖስፖርት መጠን ከ780,000 በላይ እንደነበርም ተጠቅሷል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት 3 ወራት ከሰጠው አገልግሎት 11 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 10.5 ቢሊዮን ብር እንዳሰበሰበ እና ይህም የእቅዱን 96 በመቶ እንደሆነ ተናግሯል።
የሪፖርቱን ማብቃት ተከትሎ ጥያቄ የጠየቁት አቶ ሳዲቅ አደም የተባሉ የምክር ቤት አባል የተቁሙን የቁጥጥር አቅምን ማደግ አድንቀው በሩብ ዓመት የተሰጠው የፓስፖርት አገልግሎትም የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሳዲቅ “ነገር ግን ተቋሙ ከተሰጠው ሃላፊነት አንጻር ወደ ገቢ መሰብሰብ አላመዘንም ወይ “ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ወደ 11 ቢሊዮን ለመሰብሰብ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ማቀዱን ያስታወሱት የምክር ቤት አባሉ የገልግሎቱ ቀዳሚ ግብ ገቢ መሰብሰብ ነው ወይስ? አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ነው ካሉ በኋላ ማብራርያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
አገልግሎቱ ገቢ ላይ ትክረቱን አድርጓል በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የምንሰጠው አገልግሎት ስለሆነ በዚህም ብዙ ገንዘብ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡
የተቋሙ ባህሪ አገልግሎት መስጠት ነው በዚህም በተለያ የውጭ አገር ሰዎች ሲመጡ ቪዛ እንሰጣለን ይህ አገልግሎት ደግሞ በየትኛውም አለም በገንዘብ የተተመነ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በግባችን መሰረት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እና ወደ ብሔራዊ ቋት ማስገባት ካልቻልን የተቋሙን አቅም ማሳደግ እንችላለን ማለት አንችልም ብለዋል ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፡፡
የተቋሙ ገቢ ባደገ ቁጥር ለራሱም የሚጠቀመው ከሚሰበስበው ስለሆነ ሁሌ የሚለምን ተቋም መሆን የለበትም ምክንያቱ ደግሞ ቴክኖሎጂው በየጊዜው ስለሚቀያየር ሲሉ እራሱን ማሻሻል እንዳለበት ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም በመንግስት ስም አገልግሎቱ ገቢ እንደሚሰበስብ የተናገሩት ወ/ሮ ሰላማዊት እኛ ያደረግነው የቀድሞውን ወይንም የነበረውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ነው ብለዋል፡፡
ሰዎች ብዙ ጊዜ ገቢው የሚሰበሰበው ከፓስፖርት ይመስላቸዋል እሱን ግን ስህተት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ከገቢው ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ግን ከቪዛ እና ተያያዥ አገልግሎቶች መሆናቸውን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ከ3,400 በላይ የውጭ አገር ዜጎች መያዛቸውንም የተያዙ አገልግሎቱ ጠቁሟል፡፡
ከዚህ ውስጥ ሊወጡ ሲሉ የተያዙት 1,500 በላይ ሲሆኑ፤ ከ10,900 በላይ ኢትዮጵያውን ደግሞ በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ ባለፉት 3 ወራት ተይዘዋል ተብሏል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








