top of page

የአዲስ ቄራዎች ድርጅት አካባቢውን መበከል ካላቆመ ካለበት ቄራ አካባቢ እንዲነሳ የሚል የፍርድ ውሳኔ አፈፃፀም እንደተከፈተበት ተሰምቷል

  • sheger1021fm
  • Nov 14, 2025
  • 2 min read

ህዳር 5  2018 

 

አካባቢን በመበከል በነዋሪው ላይ የጤና ጉዳት እያደረሰ ነው በሚል ክስ ቀርቦበት የነበረው የአዲስ ቄራዎች ድርጅት አካባቢውን መበከል ካላቆመ ካለበት የቄራ አካባቢ እንዲነሳ የሚል የፍርድ ውሳኔ አፈፃፀም እንደተከፈተበት ተሰምቷል፡፡

 

ቄራዎች ከአካባቢው ይነሳል አይነሳም የሚለውን ለመወሰን ለፊታችን ህዳር 15 በፍርድ ቤት ቀጠሮ ተሰጥቷል ተብሏል፡፡

 

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ከ30 ዓመታት በላይ አጥንት፣ደም፣ ቁርጥራጭ ስጋና መሰል የእርድ ተረፈ ምርቶችን በመልቀቅ አካባቢውን ሲበክል ቆይቷል በሚል ቁም ለአካባቢህ በተባለው ሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በሰጠው ውሳኔ የቄራዎች ድርጅት በሚለቅቀው በካይ ፈሳሽ፣ጠጣርና ጋዝ የነዋሪው ጤና ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ድርጅቱ አገልግሎት ከሚሰጥበት የቄራ አካባቢ እንዲነሳ፤ወይም አካባቢውን መበከሉን እንዲያቆም  የፍርድ ውሳኔውን ባሳለፍነው ጥቅምት 20 ቀን 2017ዓ.ም ነበር ያስተላለፈው፡፡

 

የፍርድ ውሳኔ ከተሰጠ ዓመት ቢሞላውም መስሪያቤቱ ፈጥሯል የተባለውን ችግር  አስተካክሎ አካባቢውን ከመበከል ባለመቆጠቡ እንዲሁም በውሳኔው መሰረት አለማስተካከሉን ተከትሎ ከአባባቢው ባለመነሳቱ፤ በፍርድ ውሳኔው መሰረት በድርጅቱ ላይ አፈፃፀም መክፈቱን ከሳሹ ቁም ለአካባቢህ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ነግሮናል፡

 

በክርክሩ ሂደት ተከሳሹ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በፊት ከነበረው አንፃር አሰራሩን እያሻሻለ በአካባቢው የሚፈጠረውን ሽታም ይሁን በካይ ፍሳሽ ቆሻሻ መቀነሱን ጠቅሶ እንደተከራከረ የነገሩን የድርጅቱ መስራችና ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ኦጎ ናቸው፡፡

 

እውነት ነው ከነበረው ብክለቱ ሊቀንስ ይችላል ነገር ግን አሁን ያለውም ቢሆን ለአካባቢው ነዋሪ የጤና ጠንቅ ነው ይላሉ፡፡

 

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ዓመት አሳልፎት በነበረው ውሳኔ የአካባቢ ብክለቱን ለማቆም የተጠቀመውን መሳሪያ ወይም ቴክኖሎጂ ግልፅ በሆነ ሙያዊ ማብራሪያ ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዳ ሲል ፍርድ ቤቱ የአፈፃፀም መመሪያ ሰጥቶ ነበር፡፡

 

ጉዳዩን አስመልክቶ የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው ጉዳዩ በሂደት ላይ ነው በሚል  ስለ ክርክሩ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

 

ይሁንና እንደ አጠቃላይ የመስሪያ ቤቱን ስራ የሚያዘምን ነው ያሉትና 65 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የተረፈ ምርት ማቀነባበሪያ ማሽን ከውጭ ማስመጣታቸውንና የተከላ ስራ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 

ማሽኑ ስራውን ሲጀምር አካባቢውን የሚበክለው ሽታይኖርም ብለዋል፡፡

 

የፍሳሽ አወጋገዳችንንም አስተካክለናል በማለት ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ወደፊት እንሰጣለን ብለውናል፡፡

 

በፍርድ ውሳኔው መሰረት በካይ የሆነውን መጥፎ ጠረን ያስወግዳል የተባለውን አዲሱ የተረፈ ምርት ማቀነባበሪያ ማሽን ጥቅም ላይ በማዋል ሌላውንም አይነት ብክለት እንዴት ባለ መልኩ እንዳስወገደ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ ማስረዳት ይኖርበታል ተብሏል፡፡

 

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….

 

ምንታምር ፀጋው

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page