የአስር እና አምስት ብር ኖቶችን ልክ እንደ ሳንቲሞች ሁሉ የዋጋ ንረት እየበላቸው፣ ከገበያም እየወጡ ይሆን?
- Feb 26
- 2 min read
የካቲት 19/2018
የአስር እና አምስት ብር ኖቶችን ልክ እንደ ሳንቲሞች ሁሉ የዋጋ ንረት እየበላቸው፣ ከገበያም እየወጡ ይሆን?
የገንዘቦች መነሻ የሆነው ሳንቲም በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ አቅም አጥቶ ተዳክሞ ከወጣ አመታት ተቆጥሯል፡፡
አንድ ብርም የሚገዛው ነገር የለም፤ የአስር እና አምስት ብር የመግዛት አቅምም በእጅጉ አሽቆልቁሏል፡፡
አሁን በአገሪቱ ገበያ ውስጥ ያለው የሚዘዋወረው የአስር እና አምስት ብር ኖትም ያረጀ፣ የተቀዳደደ፣ በማያያዣ የተለጣጠፈ እና በምልልስ የሳሳ መሆኑ ይታያል።
የምጣኔ ሀብት እና የፋይናስ ባለሙያዎች የዋጋ ግሽበቱ ሁለቱን ገንዘቦች እየበላቸው እና ከገበያ እያወጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የሁለቱ የገንዘብ ኖቶች አዲስ ህትመትም በገበያ ውስጥ እየታየ አይደለም ፤ይህስ ለምን ሊሆን ቻለ ? የአስር እና አምስት ብር የገንዘብ ኖቶች ከገበያ መውጣትስ በዋጋ ንረት ላይ የሚያሳድርው ተጽዕኖ ምንድነው?

ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱን የጠየቅናቸው የፋይናንስ ባለሙያ እና የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ከፈለኝ ሃይሉ የዋጋ ግሽበቱ የገንዘቦቹን የመግዛት እቅም እያሳጣ እንደሆነ አስረድተው በዚህ ምክንያት የአስር እና አምስት ብር እጣፋንታም እንደ ሳንቲሞች እየሆነ መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን ይገልፃሉ።
የእነዚህ ብሮች ከገበያ መውጣት ደግሞ የዋጋ ንረትን እንደሚያባብስ አቶ ከፈለኝ አስረድተዋል፡፡
ባለሙያው "ከአንድ አመት በፊት የገንዘብ መጀመሪያው አስር ብር ሆኖ እንደ ነበር ጠቅሰው አሁን ወደ ሃምሳ እና መቶ ብር እየሆነ ነው" ብለዋል፡፡
ከታች ያሉት ገንዘቦች የመግዛት አቅማቸው በወረደ ቁጥር የዝቀተኛው የብር ህትመት ወደ ላይ ስለሚሆን የሚያድገው የዋጋ ንረቱን እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ።
የሁለቱ የብር ኖቶች መጥፋት የዋጋ ንረትን ሊያባብስ እንደሚችልም አቶ ከፈለኝ ነግረውናል፡፡
ሌላው የምጣኔ ሃበት ባለሙያ መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) የፍጆታም ሆነ ሌሎች የሚሸመቱ እቃዎች ዋጋቸው እየናረ በመምጣቱ የአስር እና የአምስት ብር የመግዛት አቅም በእጅጉ እየተመናመነ መምጣቱን ጠቅሰው አሁን በገበያ ያለው የእነዚህ ብር ኖቶች "ጥራቱም የቀነሰ እና እየወረደ ነው" ብለዋል፡፡
በማዕከልም እስካሁን አዳዲስ የብር ኖቶች በገበያ ላይ ባለመኖራቸው ምክንያት "ምናልባት ያሉትን የብር ኖቶች መነሻ ከፍ ለማድረግ ታቅዶ ሊሆን ይችላል" የሚል ግምት እንዲኖረን ያደርጋል ብለዋል።
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments