የነሐሴ 9 የውጪ ሀገር ወሬዎች
- 2 days ago
- 2 min read
የኮንጎ ኪንሻሣው የኢቦላ ወረርሽኝ አድማሱን እያሰፋ ነው ተባለ፡፡
ወረርሽኙ ወደ ተጨማሪ ግዛትም መዛመቱን የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ /አፍሪካ CDC/ መረጃ ማሳየቱን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
በኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ያዳረሳቸው ግዛቶች ብዛት 6 ደርሷል፡፡
ኢቱሪ ወረርሽኙ ከፍተኛ ጫና ያሳደረባት ግዛት ነች፡፡
ወረርሽኙ መቀስቀሱ ከተነገረ 3 ወር ሆኖታል፡፡
እስከ ትናንትም የገደላቸው ሰዎች ብዛት 2 ሺህ 100 ደርሷል፡፡
የኮንጎው ኢቦላ በከፍተኛ የመዛመት ፍጥነት ላይ ነው፡፡
በታሪክም ታላቁ የኢቦላ ወረርሽኝ ሊሆን የሚችልበት እድል የሰፋ ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭለድሚር ፑቲን በቀጠናዊ የፀጥታ እና ደህንነት ጉዳይ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በትብብር እንሰራለን አሉ፡፡
ፑቲን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ቀጠናዊ የፀጥታ እና የደህንነት ጉዳዮች ተባብረን እንሰራለን ያሉት ኮሪያ ከጃፓን ወረራ ነፃ የወጣችበትን 81ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት እንደሆኑ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በደም ማህተም የተሳሰረ ነው ብለዋል፡፡
ኮሪያን ከጃፓን ወራሪዎች ነፃ ለማውጣት በዘመኑ ሩሲያም አባል የነበረችበት የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ከፍተኛ የጦር ተሳትፎ ነበራት፡፡
በአሁኑ ወቅት ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ በመካከላቸው ወሰን አልባ የትብብር ስምምነት እንዳላቸው መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ የባህር መተለላፊያ ወሽመጥን የአሜሪካ የግዛት አካል አደርገዋለሁ አሉ፡፡
ትራምፕ ትንሽ ጠብቁኝ እንጂ ሆርሙዝን የአሜሪካ አካል እንደማደርገው ታዩታለች ማለታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በየትኛው ህግ እና አግባብ እንደሆነ ግን የአሜሪካው ፕሬዘዳንት የጠቀሱት ነገር የለም፡፡
የኢራኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ የኢራን የማይነጠል የግዛት አካል ሆኖ ይዘልቃል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ቀደም ሲል አሜሪካ እና ኢራን በተፈራረሙት የጦርነት ማስቆሚያ የመግባቢያ ስምምነት ወዲህ በሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ እልህ እየተጋቡ ነው፡፡
ጋሪባባዲ ወሽመጡን ዝግ አድርገነው እንቆያለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
ከኢራኑ ጦርነት በፊት ሌላ ሌላውን ሳይጨምር የሆርሙዝ ወሽመጥ የ20 በመቶው የአለማችን የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ማለፊያ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
ኢንዶኔዥያ በከባድ የመሬት ነውጥ ተመታች፡፡
ፍሎሬስ የተባለውን ግዛት የመታው ነውጥ በርዕሰ መሬት መለኪያ /ሬክተር ስኬል/ 7 ነጥብ 7 ሆኖ መመዝገቡን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ነውጡን ተከትሎ ሱናሚ የተሰኘው ከባድ የባህር ማዕበል ሊቀሰቀስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተሰምቷል፡፡
በዚህም የተነሳ የባህር ዳርቻ እና የዝቅተኛ ስፍራዎች ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ወደ ከፍተኛ ስፍራዎች እንዲዛወሩ ተመክረዋል፡፡
ነውጡ በርካታ ሕንፃዎችን እና ቤቶችን ደረማምሷል ተብሏል፡፡
በአደጋው በጥቂቱ የ2 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡
ከነውጡ ሰፊ አካባቢን ማዳረስ አንፃር የአደጋው ሟቾች እና ተጎጂዎች ብዛት ሊጨምር እንደሚችል ተፈርቷል፡፡
ኢንዶኔዥያ የመሬት ነውጥ እና እሳተ ገሞራ የሚደጋገምባት አገር እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
_edited.jpg)



Comments