የነሐሴ 5 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች
- 4 hours ago
- 2 min read
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በጦርነቱ ለተገደሉብን ወታደሮቻችን ካሣ ልትከፍል ይገባል አሉ፡፡
ቀደም ሲል በጦርነቱ አሜሪካ ላደረሰችባት ጉዳት ሁሉ ካሣ እንዲከፈላት የጠየቀችው ኢራን እንደነበረች አልጀዚራ አስታውሷል፡፡
ትራምፕ የተገደሉባቸው የጦር ባልደረቦች ብዛት ባይጠቅሱም እኛም ለተገደሉብን ሰዎች ካሣ እንጠይቃለን ሲሉ በትሩዝ ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ እወቁልን ብለዋል፡፡
ትራምፕ አልፈው ተርፈውም የኢራን መንግስት ባለፉት 50 አመታት ለገደላቸው የተቃዋሚዎች ቤተሰቦች ጭምር ካሣ ሊከፍል ይገባዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ተደራዳሪዎቻቸው የካሣ ጥያቄያቸው በወደፊቱ ንግግር በአጀንዳነት እንዲያሲዙላቸው ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡
አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል ከተተኮሱ በኋላ አቅጣጫ የመቀያየር ብቃት ያላቸው ሚሳየሎች አሉን አለ፡፡
ይሄም ብቃት ሚሳየሎቻችን ከጠላት የሚሳየል መከላከያዎች በቀላሉ እንዲያመልጡ ያስችላቸዋል ማለቱን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
የአብዮታዊ ዘቡ ቃል አቀባይ ሁሴን ሞሐቢ ሚሳየሎቻችን በሙሉ ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ አድርጋችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ቃል አቀባዩ ሚሳየሎቻችን በጦር ቴክኖሎጂ ረቀቅ ያሉ እና የማውደም ብቃታቸውም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ኢራን እና አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በጦር መጠቃቃታቸውን ጋብ ቢያደርጉትም ሊያገረሽ ይችላል የሚለው ስጋት ግን እንዳለ ነው፡፡
ቀደም ሲል ኢራን በአሜሪካ ሲሰነዘርባት ለነበረ የጦር ጥቃት በአቅራቢያው አገሮች በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ተቋሞች ላይ የአፀፋ ጥቃት ስትሰነዝር እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
የግሪክ የሰደድ እሳት ተከላካዮች አዲስ ከተቀሰቀሰ ቃጠሎ ጋር እየታገሉ ነው ተባለ፡፡
ኣዲሱ የሰደድ እሳት የተቀሳቀሰው በርዕሰ ከተማዋ አቴንስ ደቡብ ምስራቅ ክፍል እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡
በሰዓት 70 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት የሚጋልብ ነፋስ የሰደድ እሳቱን አድማስ ለመገደብ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል፡፡
የሰደድ እሳቱን የማጥፋቱ ተግባር በቃጠሎ ተከላካይ አውሮፕላኖች እና ሔሊኮፕተሮች መታገዙ ታውቋል፡፡
ንፋሱ በመጪዎቹ ቀናት ፍጥነቱ በሰዓት እስከ 130 ኪሎ ሜትር ሊደርስ እንደሚችል በመተንበዩ የአቴንስ አቅረቢያውን የሰደድ እሳት ለመቆጣጠር ቢያንስ ተጨማሪ 5 ቀናት እንደሚጠይቅ ተገምቷል፡፡
አንደ ፈረንሳይ እና ስፔን ያሉ አገሮች በከባድ የሰደድ እሳት ሲፈተኑ የሰነበቱ የአውሮፓ አገሮች እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡
የቱርክ ፓርላማ ለቀድሞዎቹ የPKK አማጺ ቡድን ታጣቂዎች ይቅርታ ማድረግ የሚያስችል ህግ አፀደቀ ተባለ፡፡
PKK ከቱርክ የተነጠለች ኩርዲስታንን በነፃ አገርነት ለመስረት ለ40 አመታት ያህል በትጥቅ አመፅ ላይ የቆየ ድርጅት እንደነበር አልጀዚራ አስታውሷል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት የቡድኑ መሪ አብደላ ኦቻላን PKK ትጥቅ እንዲፈታ ጥሪ ያቀረቡት ከአመት ከመንፈቅ በፊት ነበር፡፡
ቡድኑም የትጥቅ አመፅ እርም ይሁንብኝ ያለው ወዲያውኑ ነው፡፡
የህጉ መፅደቅ በአገሪቱ ሰላም ለመውረዱ አመላካች እርምጃ ነው ተብሏል፡፡
የይቅርታ ህጉ በእስር ላይ የሚገኙ 3 ሺህ 500 ያህል የቀድሞው አማጺ ቡድን ታጣቂዎች እንዲፈቱ የሚያስችል እንደሆነ ታውቋል፡፡
የኔነህ ከበደ
_edited.jpg)



Comments