የነሐሴ 2 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች
- 2 days ago
- 2 min read
ዩጋንዳ በአለም አቀፉ አረጋጊ ሀይል ማዕቀፍ ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ሰርጥ ልትልክ ነው፡፡
የምስራቅ አፍሪካዊቱ አገር ፓርላማ የዩጋንዳ ወታደሮች በጋዛ በአረጋጊነት እንዲሰማሩ ድምፅ መስጠቱን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዛ ሰላም ያቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች እቅድ በሰርጡ አለም አቀፍ አረጋጊዎች እንዲሰፍሩ ይጠይቃል፡፡
ሐማስን እና ሌሎች የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቅ የማስፈታቱ ድርሻ የአረጋጊው ሀይል ነው ተብሏል፡፡
ከዩጋንዳ በተጨማሪ ሞሮኮም ወደ ጋዛ አረጋጊ ወታደሮችን ለመላክ ቃል የገባች አፍሪካዊት አገር እንደሆነች ታውቋል፡፡
ዩጋንዳ ለአረጋጊው ሀይል ወታደሮችን እንድትልክ ትጠየቅ ፤ አትጠየቅ ለጊዜው በግልፅ የታወቀ ነገር እንደሌለ ተጠቅሷል፡፡
የሳውዲ አረቢያ ፣ የቱርክ እና የፓኪስታን መሪዎች የጋራ የመከላከያ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
በመካ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት የጋራ መከላከያ ስምምነቱን የሳውዲው አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ፤ የቱርኩ ፕሬዘዳንት ሬቺፕ ታይፕ ኤርዶጋን እና የፓኪስታኑ ሼህቫዝ ሻሪፍ እንደፈረሙት አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ስምምነቱን የመካው ስምምነት ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ሰነዱ በአንዷ ላይ የጦር ጥቃት ቢሰነዘር ሌሎቹም ለመከላከሉ በጋራ እንዲሰለፉ ይጠይቃል ተብሏል፡፡
በአንዱ አገር ላይ የተሰነዘረ ጥቃትም በሁሉም ላይ እንደተፈፀመ እንደሚቆጥሩት ተጠቅሷል፡፡
ያም ሆኖ ስምምነቱ የመከላከል እንጂ የአጥቂነት ዓላማ የለውም ተብሏል፡፡
ስምምነቱ የጦር ቴክኖሎጂ ትብብርንም እንደሚመለከት መረጃው አስታውሷል፡፡
በኮንጎ ኪንሻሣ በኢቦላ የሚያዙ ሕሙማን ብዛት በጣሙን እየጨመረ ነው ተባለ፡፡
በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ብዛት ከ4 ሺህ መብለጡን አናዶሉ ፅፏል፡፡
የሟቾች ብዛትም ከ1 ሺኅ 800 በላይ ሆኗል፡፡
የወረርሽኙም አድማስ እየሰፋ ነው ተብሏል፡፡
ኢቱሪ የተባለችዋ ግዛት የወረርሽኙ ጫና የበረታባት ነች፡፡
በኮንጎ ኢቦላ በወረርሽኝ ደረጃ መቀስቀሱ ከተነገረ ወደ 3ኛ ወሩ ተቃርቧል፡፡
ወረርሽኙ እስካሁን ባለው የአጭር ጊዜ የመዛመት ፍጥነት በታሪክ ከተከሰቱት ሁሉ 2ኛው ታላቅ የኢቦላ ወረርሽኝ ሆኗል ተብሏል፡፡
ምናልባትም በኢቦላ የተያዙ ሰዎች ብዛት ከይፋዊ አሃዙም በላይ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡
የታይላንዱ በአገሪቱ ጥብቅ የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ ስራ ላይ አውላለሁ አሉ፡፡
የታይላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከእንግዲህ ጥብቅ የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ ይኖረናል ያሉት አንድ የ14 አመት አዳጊ ይዞት በነበረው መሳሪያ ተኩሶ 8 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ ነው፡፡
በሌሎች 22 ሰዎች ላይ ደግሞ አካላዊ ጉዳት ማድረሱ ተጠቅሷል፡፡
በመኖሪያ ቤታቸው አያቶቹን ከገደለ በኋላ ወደ ትምህርት ቤቱ በማምራት ተኩስ ከፍቶ ግድያ እና አካላዊ ጉዳት ማድረሱን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
አጋጣሚው አገሩን በእጅጉ አስደንግጧል፡፡
በስፋትም እያነጋገረ ነው ተብሏል፡፡
የኔነህ ከበደ
_edited.jpg)


Comments