top of page

የትምህርት ሚኒስቴር ከቅድመ አንደኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተመጣጠነ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እንዲተገብር ግዴታ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴ ተመራ፡፡

  • 8 hours ago
  • 2 min read

ግንቦት 28/2018


በሀገሪቱ "አሳሳቢ" ደረጃ ላይ ያለውን የመቀንጨር ችግር ለመፍታት የትምህርት ሚኒስቴር ከቅድመ አንደኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች የተመጣጠነ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እንዲተገብር ግዴታ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴ ተመራ፡፡


ረቂቅ አዋጁ በሀገሪቱ "አሳሳቢ" ደረጃ ላይ ያለውን የመቀንጨር ችግር ለመፍታት 13 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ግዴታ የሚጥል ነው፡፡


ለረቂቅ አዋጁ መተግበር ማንኛውም ሰው የመተባበርን ግዴታ እንዳለበት በረቂቁ ተደንግጓል፡፡


የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ትናንት ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ለጤና፣ ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው የምግብ ስርዓት እና የስርዓት ምግብ ረቂቅ አዋጅ ይሰኛል።


ረቂቁ የቃላቱን ትርጉም ሲያስረዳ የምግብ ስርዓት ማለት አካባቢን፣ ግብዓትን፣ አመራረትን፣ ማቀነባበርን ብክነት እና አወጋገድን አንድ ላይ የያዘ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ውጤቶን አጣምሮ ያያዘ ነው ይላል።


ስርዓተ ምግብ ደግሞ አገልግሎት እና ተግባራትን በመተግበር ማህበረሰብ ከስርዓተ ምግብ ችግር ነጻ እንዲሆን የሚስችል ስርዓት እንደሆነ ዘርዝሯል።


የረቂቁ ማብራሪያ መግቢያ ላይ መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ የምግብ ዋስትና እንዲኖራቸው በበቂ ሁኔታ ጥራት ያለው ምግብ ማግኘታቸውን የማረጋገጥ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት እንዳለበት አስረድቷል።


ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ አካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ እየሰራች እንዳለ የዘረዘረው ረቂቁ ይህን ግብ ማሳካት የሚቻለው የተስተካከለ እና የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ሲቻል ነው ብሏል።



በ2018 ዓ.ም ይፋ በተደረገው የጤናና የስነ ህዝብ ዳሰሳ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ ያሉት 40 በመቶ (6.6ሚሊዮን ) የሚሆኑት ህጻናት የቀነጨሩ መሆናቸውን ማብራሪያው አካቷል።


በተጨማሪም አሁን በአዋቂነት እድሜ ላይ ያለው አምራች ሃይል የሚገኘው 67 በመቶ የሚሆነው ከአምስት ዓመት በታች እያለ የቀነጨረ ነበር ይላል የምግብ ስርዓት እና የስርዓት ምግብ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ መግቢያ።


በሀገሪቱ ከመቀንጨር እና ስርዓት ምግብ መዛባት ጋር የተያያዙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታ መጠን መጨመር በጤና፣ ትምህርት ፣ በአካባቢው እና በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩም በረቂቁ ተመላክቷል።


ይህን ችግር ለመቅረፍ በረቂቅ አዋጁ ክፍል አራት ስር ለ13 ሚኒስቴር መስሪያቤቶች እና ለአንድ ኮሚሽን መስሪያ ቤት ከፍተኛ ሃላፊነት ተሰጥቷል።


በዚህም መሰረት የትምህርት ሚኒስቴር፤ ለሀገር በቀል ምርቶች ትኩረት በመስጠት ሁሉም የመንግስት የቅደመ አንደኛ፣ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች የተመጣጠነ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እንዲተገብር ያዝዛል።


በተጨማሪም የምግብ ስርዓት እና የስርዓተ ምግብ ስርዓትን በትምህርት ውስጥ ያካትታል፣ ትምህርት ቤቶች በንጥረ ምግብ የበለፀጉ ምርቶች እንዲመረቱ ያደርጋል እና በትምህርት ቤቶቹ በንጥረ ምግብ የበለጸጉ ምግቦችን ዝርዝርን ያዘጋጃል።


የጤና ሚኒስቴር ደግሞ የስርዓተ ምግብ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ከውጪ ባለሃብቶች ጋር ይመክራል፤ጥራቱን ይቆጣጠራል ፣ ስረዓተ ምግብ በትምህር ስርዓቱ ውስጥ እንዲካተት እንዲደግፍ፣ የቪታሚን ኤ(A) እንክብል እና ፎሊክ አሲድ አገልገሎት እንዲያገኙ ያደርጋል፣ መምህራን እና ተማሪዎች ወቅታዊ የጤና ምርመራ እንዲያገኙ የማድረግን ግዴታ ይጥላል።


በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምርቶች አንዲመረቱ የግብርና ሚኒስቴር፣ በምግብ ሴከተር የተሰማሩ አነስተኛ የንግድ ማጠናከር ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በፋብሪካ ደረጃ የሚመረቱት የምግብ አይነቶችን ጥራት መቆጣጠር ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣ ለትምህርት ቤቶቹ ንጹሁ ውሃ ማቅረብን ደግሞ ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ረቂቁ ይሰጣል።


ለትምህርት ቤት ምገባ የፋይናንስ ስርዓት እንዲዘረጋ፣ የትምህርት ቤት ምገባ የሀብት ፍላጎትን የሀገሪቱ የበጀት አዋጅ አካል እንዲደርግ ፣ ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር የሚያስፈልገውን የበጀት ርዕስ እንዲኖረው የማድረግ ሃላፊነትን ደግሞ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሰጥቷል፡፡


የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት ሃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም ተካቷል።


ረቂቅ አዋጁ በክፍል 20 ትብብርን በተመለከተም ለአዋጁ አፈጻጸም ማንኛውም ሰው የመተባበር ግዴታ አለበት ይላል።


ያሬድ እንዳሻው

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page