በምሥራቅ አርሲ ወረዳዎች በተፈጸመው ጥቃት የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ
- 7 hours ago
- 2 min read
ግንቦት 28/2018
በምሥራቅ አርሲ ወረዳዎች በተፈጸመው ጥቃት የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የተመራ ልዑክ ከሰላም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸው ተሰማ።
በተፈጸመው ጥቃት ለደረሰው ጉዳት መንግሥት የችግሩን ምንጭ አጣርቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምን እንዲያሰፍን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ መጠየቃቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ዘግቧል፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ካደረገ በኋላ በሊቀ ጳጳሳት የተመራ ከፍተኛ የቤተክርስቲያን የልዑካን ቡድን ከሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ ጋር ተወያይተዋል ተብሏል።

በምሥራቅ አርሲ በአሰኮ፣ በሽርካ፣ በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በሰዎች ላይ የሚደርሰው የሕይወት ጉዳት እና በጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን መቃጠልን በተመለከተ መንግሥት የችግሩን ምንጭ አጣርቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን አለበት ሲሉ ሊቀ ጳጳሳቱ አሳስበዋል፡፡
በችግሩ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትና መልሰው የሚቋቋሙበት ሥራ እንዲሠራ፣ ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎችም ለፍርድ ቀርበው ቅጣታቸውን እንዲያገኙ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው በመንግሥት በኩል በአስቸኳይ አጣሪ ቡድን ተቋቁም ወደ ስፍራው ተልኳል፣ የአጣሪ ቡድኑን ሪፖርት መሠረት በማድረግም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በሌላ በኩል የቤተክርስቲያኒቱ ብፁዓን አባቶች ከኦሮሚያ ፕሬዘዳንት ጽ/ቤት እንዲሁም ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል ተብሏል።

የክልሉ መንግሥት በሥፍራው የተከሰተውን ችግር ለመቆጣጠርና ሊከሰት ይችል የነበረውን ተጨማሪ አደጋን ለመከላከል መስራቱን፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ሥፍራው አጣሪ ቡድን መላኩንና ውጤቱን ተከትሎም አጥፊዎችን ለሕግ እንደሚያቀርብ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ተናግሯል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የቤተክርስቲያኗ ምዕመናንን ለማጽናናትና ድጋፍ ለማድረግ በምታደርገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግም ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክና ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፣ ሰሞኑን በአርሲ ሃገረ ስብከት በርካታ በምዕምናን ላይ የግድያ ጥቃት መፈፀሙን በጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖች መፈናቀላቸውን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ አሰቃቂ ጥቃት በቤተ ክርስቲያን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ መሆኑን ጠቅሰው የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና ሰላምን የማስፈን አደራ አለባቸው ያሏቸውን፣ የመንግስት የፀጥታ አካላትና በየመዋቅሩ ያሉ ሃላፊዎችን ጥቃቱን እንዲያስቆሙና ድርጊቱን የፈፀሙትን ለህግ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i





Comments