የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን፤ "በርካታ ከፍተቶች" እንደተገኙበት የመንግስት ወጭ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናገረ።
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 2 min read
ታህሳስ 7/2018
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን፤ የስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የውጭ አገር ስራ ስምሪት አፈጻጸምን በተመለከተ በተሰራ ኦዲት ተቋሙ "በርካታ ከፍተቶች" እንደተገኙበት የመንግስት ወጭ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናገረ።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ኤጀንሲዎችን በበቂ ሁኔታ እየተቆጣጠረ እንዳልሆ፤ ለስደት ተመላሾችም ምቹ የሆነ የስራ ቦታ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዳላደረገ ፣ ሰራተኛ ለማሰማራት ከተቀባይ አገራት ጋር ያሰረውን ውልም ወደ ስራ ማስገባት እንዳልቻለ የክዋኔ ኦዲቱ አረጋግጧል፡፡
ይህ የተነገረው በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ዋና ኦዲተር ከ2014 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ያቀረበውን የኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ የተቋሙን አፈጻጸም በትናንትናው እለት ባደመጠበት ወቅት ነው፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳዳር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን ጥያቄ ያቀረቡት ወ/ሮ እየሩሳሌም ሴቶች ፣ አካል ጉዳተኞች እና ከስደት ተመላሽ ስራ ፈላጊዎች ቅድሚያ የስራ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ቢኖርም ምቹ የስራ ቦታ እና ገንዘብ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው አስታውሰው ይህም አፈጻጸም ከተያዘው እቅድ አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰራተኛ ወደ ውጭ ለመላክ ከተቀባይ አገራት ማለትም ከኩዌት ፣ከጀርመን ኮንስትራክሽን ፌደሬሽን እና ከስዊድን ድርጅት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ማደረጉን የተናገሩት ወ/ሮ እስካሁን ለምን በስምምነቱ መሰረት ሰራተኞችን እንዳልተላኩም ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ኤጀንሲዎችን በአዋጁ መሰረት የተጣለባቸውን ሃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በተሰራ የክዋኔ ኦዲት በቂ ክትትል እንዳላደረገ የተናገረው ቋሚ ኮሚቴው ይህም ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡
ከኩዌት ጋር የተደረገውን ስምምነት በተመለከተ ከዚህ በፊት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅም በላይ የነበረ ችግር በመኖሩ ወደ ተግባር ስምምነቱን ማስገባት እንዳልቻለ ተናግሮ አሁን ግን ችግሩን በዲፕሎማሲ ተነጋግሮ መፍታት ተችሏል፡፡
በርካታ ሰራተኞችም አሁን በኩዌት ተሰማርተው ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ለስደት ተመላሽ ፣ ለሴቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ በእቅዳችን መሰረት አቅደን እየሰራን ነው ሲሉ ሚኒስቴር ዴዔታው አቶ ሰለሞን ሶካ መልሰዋል፡፡
ከስደት ተመላሾች ላይ ተቋሙ ያቀደውን ያክል ባይሆንም የተቻለውን ያክል እየሰራ እንዳለ የተናገሩት አቶ ሰለሞን አገሪቱ በቀጠናው ካሉ አገራት የተሻለ ስራ በመሰራቱ በኢጋድ አባል አገራት መድረክ ላይ ተሞከሮዋን አካፍላላች ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስራ ጀማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ እና ብድር የሚያገኙበት ሥርዓት የተመቸ ስላልሆነ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ይህን ሊግዝ የሚችል ፖሊሲ ባለፈው አመት መጽደቁን ያስረዱት አቶ ሰለሞን ይህንኑ ችግር ለመፍታት በዚህ በጀት አመት ሁለት አዋጆች እንደሚጸድቁ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ኦዲትር በበኩሉ መልሱ ተለይቶ ለእያንዳንዱ መመለስ ሲገባው ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች በኩል የተሰጠው መልስ “አራንባ እና ቆቦ” የረገጠ ነው ብሏል፡፡
የመስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎችም የሰጡት ምላሽ ሪፖርቱን በአግባቡ እንዳላነበቡት ያሳያል ሲሉ የክዋኔ ኦዲት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሃጂ ኢብሳ ኦዲቱ የተሰራው አገሪቱ በሌላት ገንዘብ መሆኑን ተናግረው አንደ አመት ሙሉ የፈጀን ስራ መስሪያ ቤቱ የተረዳበት መንገድ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ተቋሙ ከጀርመን እና ስዊድን ጋር ውል ያሰረውን የስራ ስምምነት ወደ ተግባር ማስገባት እንዳልቻለ ሃጂ ኢብሳ አስረድተዋል፡፡
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሰራሁት ላለው ስራ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉ ተገቢ እንዳልሆነ የኦዲተር መስሪያ ቤት ተናግሯል፡፡
ለስደት ተመላሾች የስራ እድል ለመፍጠር ከአቀደው ማሳካት የቻለው 37 በመቶ ብቻ እንደሆነ እንዲሁም ለ2 መቶ ኤጀንሲዎች ቅድመ ፍቃድ እድሳት ቆጠራ ላማካሄድ ታቅዶ መስጠት የተቻለው 42 ብቻ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈርያ ካሚል መስሪያ ቤቱ በአዲስ መልክ ሥርዓት እየዘረጋ እንዳለ እና የተነሱ ችግሮች ደግሞ ከተቋሙ አለመስራት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ያለው የስራ ፍላጊ ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በኦዲተር መስሪያ ቤት የተለዩ ችግሮችን እንዲያርም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አሳስቧል።
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1








