top of page

በኢትዮጵያ አሁን ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል ብክነት

  • sheger1021fm
  • 2 minutes ago
  • 2 min read

ታህሳስ 6 2018

 

በኢትዮጵያ ከሚመረተው የኤሌክትሪክ ሀይል ከ20 እስከ 30 በመቶው ይባክናል፡፡ ይህም በአለም ላይ ከሚስተዋለው ከ8 እስከ 9 በመቶ ጋር ሲተያይ ከፍተኛ ነው፡፡

 

የሀይል ስርቆት ፣ የመሰረተ ልማት ችግሮች ለሀይል ስርቆት በዋና ምክንያትነት ይነሳሉ፡፡

 

በኢትዮጵያ አሁን ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል ብክነት ግልገል ጊቤ 3 ከሚያመነጨው ኃይል ጋር  የተቀራረበ እንደሆነ ይነገራል።

 

እስካሁን በኃይል ብክነት ዙሪያ የተሰሩ ተብለው የሚወጡት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብክነቱ አነስ ሲል 890ሜጋ ዋት፡ ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ ከ1200 ሜጋ ዋት በላይ ነው።

 

ይህ ማለት ከሚመረተው ኃይል ከ21 እስከ 30 በመቶው ባክኖ ይቀራል።

 

ጥናቶቹ ይህን ያህል መጠን ይባክናል ተብሎ ይገመታል ከማለት በዘለለ ለምን ይሆን ትክክለኛውን መጠን ማስቀመጥ ያልቻሉት?

 

በየትኛው ዘርፍ ምን ያህል ባከነ? ብክነቱ በገንዘብ ቢሰላ ምን ያህል ያሳጣን ይሆን? የሚለውን ጠይቀናል።

 

አቶ አብዱረዛቅ  ጀማል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮጀክት  ኤክስፐርት ናቸው።

 

ጥናቶቹ የሃይል ብክነት እንዳለ ማሳያ አድርገን እንጠቀምባቸው እንጂ በመላው ሃገሪቱ ምን ያህሉ የኤሌክትሪክ ሃይል ጥቅም ላይ ዋለ? ምን ያህሉስ ባከነ የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱ አይደሉም ይላሉ።

 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ባሏት 22 የኃይል ማመንጫዎች 8115 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ፈጥራለች፤ ከዚህም ውስጥ ባለፈው ዓመት 7910ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨቷን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያሳያል።

 

ከዚህ ውስጥም ብክነቱን ለማስላት ትንሹን የ20በመቶ ብክነት እንኳን ብንወስድ ከተመረተው 7910ሜጋ ዋት ኃይል 1ሺህ582ቱ ሲባክን 6328ቱ ሜጋ ዋት ኃይል ደግሞ ጥቅም ላይ ውሏል ማለት ነው።

 

አቶ አብድረዛቅም ብክነት እንዳለ እሙን  ነው ነገር ግን ብክነቱ የትና እንዴት ይፈጠራል?

 

ለመቆጣጠር ምንስ መደረግ አለበት?

 

የሚለውን በውል ለማወቅ ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ የሚለን ጊዜ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

 

አገልግሎቱ ከዚህ ጉድለት በመነሳት ብክነትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎች እያለማ ይገኛል ተብሏል።

 

ቴክኖሎጂዎቹ በየትኛው አካባቢ ምን ያህል ኃይል እንደሚያስፈልግና  አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ምን ያህል ኃይል መለቀቅ እንዳለበት ቀድሞ የሚያሳውቅ ነው፡፡

 

በተጨማሪም ለተጠቃሚው ማህበረሰብ መተግበሪያ  ይኖራል፤ በመተግበሪያውም በሰዓት የተከፋፈለ   የክፍያ ታሪፍ ይኖራል፤ ጠዋት ከሰዓትና ማታ የሚኖረው ታሪፍ እንደየአጠቃቀሙ  የተለያየ መሆኑ ተጠቃሚው በሚመቸው ሰዓት የክፍያ መጠኑን እያየ እንዲጠቀም እድል ይሰጣል ተብሏል።

 

ቴክኖሎጂዎቹ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የ20 ሚሊዮን ዶላር ብድር እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዱረዛቅ በቅርቡ ወደ ስራ ሲገቡ ትክክለኛውን የብክነት መጠን መለየት ይቻላል፤ ለየማከፋፈያ ጣቢያው የሚያስፈልገውን ያህል ኃይል መልቀቅ ስለሚቻል በመሃል የሚባክነው ይቀንሳል ተብሏል።

 

በመላው ሃገሪቱ እየተከወነ ያለው ያረጁ መስመሮችን በአዲስ የመቀየር ስራም በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን ብክነት እንደሚቀንስ ከሃላፊው ሰምተናል።

 

የኃይል አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የሚረዳ ስትራቴጂ ማውጣቱን የነገረን የኢነርጂና ነዳጅ ባለስልጣን የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪና አምራቾችን ኢነርጂ አጠቃቀም ኦዲት በማድረግ እንዲሁም ሃይል የሚያባክኑ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የቤት ውስጥ እቃዎች  ኃይል ቆጣቢ ሆነው ተሻሽለው እንዲመረቱ  በማድረግ የሚባክነውን ሃይል ለመቀነስ እየሰራ እይደሆነ ነግሮናል።

 

የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት በየሃገሩ ያለ ችግር ነው የተባለ ሲሆን በዓለም ዙሪያ በምርትና ስርጭት ወቅት የሚደርስ አማካኝ ብክነት ከ8እስከ9 በመቶ ነው፤

እዚህ አማካይ ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያ የኃይል ቁጠባ ላይ ገና ብዙ መስራት ይጠበቅባታል ተብሏል።

 

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….

 

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

  

Recent Posts

See All
በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ወደ ቀድሞ ቄያቸው ምስራቅ ወለጋ ጉብሰዮ ወረዳ የተመለሱ ከ141 በላይ አባዎራዎች ድጋፍ ስለተቋረጠባቸው መቸገራቸውን ተናገሩ፡፡

ታህሳስ 6 2018 በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ወደ ቀድሞ ቄያቸው ምስራቅ ወለጋ ጉብሰዮ ወረዳ የተመለሱ ከ141 በላይ አባዎራዎች ድጋፍ ስለተቋረጠባቸው መቸገራቸውን ተናገሩ፡፡ የአካባቢው ቡሣ ጎኖፋ ወይም የእርዳታ ማስተባበሪያ በበኩሉ ድጋፍ እንዲቀጥል ለሚመለከተው የበላይ አካል ባሳውቅም ድጋፍ ግን ሊቀጥል አልቻለም

 
 
 
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page