top of page

የሰኔ 19 /2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • 1 day ago
  • 2 min read


የተለያዩ የአለማችን አገሮች በመንታ ርዕደ መሬት የተመታችዋን ቬኒዙዌላን አይዞሽ ፣ ከጎንሽ ነን እንደግፍሻለን አሏት፡፡


ቬኒዙዌላን ለመደገፍ ከጎንሽ ነን ካሏት መካከል አሜሪካ እና ካናዳ ይገኙበታል፡፡


የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አገራቸው ታላቅ ፣ ፈጣን እና ውጤታማ የእርዳታ ምላሽ ትሰጣለች ማለታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ አገራቸው በአደጋው ጉዳት ለገጠማቸው ቬኒዙዌላውያን ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እየተሰናዳች መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በአደጋው ክፉኛ ማዘናቸውን እወቁልኝ ብለዋል፡፡


ድርጅቱ ለቬኒዙዌላ አለም አቀፍ እርዳታ እንደሚያስተባብር ጉቴሬዝ አረጋግጠዋል።


የካራካስ አለም አቀፍ ኤርፖርት በአደጋው ምክንያት መዘጋቱ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱን ሊያስተጓጉለው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡


የቬኒዙዌላው መንታ ርዕደ መሬት የገደላቸው እና አካላዊ ጉዳት ያደረሰባቸው ሰዎች ብዛት እየጨመረ ነው ተባለ፡፡


የመሬት ነውጡ እስከ ትናንት ምሽት የገደላቸው ሰዎች ብዛት 235 መድረሱን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


4 ሺህ 300 ሰዎች ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ታውቋል፡፡ የነፍስ አድን ጥረቱም እንደቀጠለ ነው ተብሏል፡፡


አገሪቱ በአንድ ደቂቃ ልዩነት በርዕደ መሬት መለኪያ /ሬክተር ስኬል/ 7 ነጥብ 1 እና 7 ነጥብ 5 በሆኑ ነውጦች መመታቷን መረጃው አስታውሷል፡፡


ነውጡ በሰዎች ላይ ካስከተለው ሞት እና የአካል ጉዳት በተጨማሪ መጠነ ሰፊ የንብረት ጥፋትም አድርሷል፡፡ ከ100 በላይ ህንፃዎች መፈራረሳቸው ታውቋል፡፡ 250 ሕንፃዎች ደግሞ ጉዳት እንደገጠማቸው ተጠቅሷል፡፡



የተባበሩት መንግስታት የባህር ጉዳዮች ተከታታይ አካል በሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ መቆየት ምክንያት መተላፊያ አጥተው የቆዩ መርከቦች ከነባሕረኞቻቸው በሰላም ለማሳለፍ ጀምሮት የነበረውን ውጥን ለጊዜው ትቼዋለሁ አለ፡፡


የባህ ጉዳዮች ተከታታይ አካሉ ውጥኑን በጊዜያዊነት ለመተው የተገደደው አንዲት መርከብ በኦማን ባህረ ሰላጤ ጥቃት ከተሰነዘረባት በኋላ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡


በመርከቧ ላይ ጥቃት ተሰነዘረባት በአጥቂ ሰው አልባ በራሪ አካል /ድሮን/ ነው ተብላል፡፡

ጥቃቱ በማን እንደተሰነዘረ በግልፅ አልተጠቀሰም፡፡


በመርከቧ ላይ የደረሰውም ጉዳት በዝርዝር አልታወቀም፡፡


በጦርነቱ ምክንያት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ በመቆየቱ ከ600 ያላነሱ መርከቦች ከነ 11 ሺህ ባሕረኞቻቸው ጋር መተላለፊያ አጥተው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


የባህር ጉዳዮች ተከታታዩ አካል መርከቦቹን ከነባሕረኞቻቸው በሰላም ማስወጣት የጀመረው ካለፈው ማክሰኞ አንስቶ ነበር፡፡


አሁን ግን ይሄን ተልዕኮዬን ለማቋረጥ ተገድጃለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ከቀናት እፎይታ በኋላ የሆርሙዝ መወዛገቢያነት ማገርሸቱን መረጃው አስታውሷል፡፡



የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሣ በስደተኞች ላይ አነጣጥሮ የሚፈፀምን ጥቃት አንታገስም አሉ፡፡


ራማፎሣ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት መንግስት በአገሪቱ የሚገኙ የውጭ አገር ሰነድ አልባ ስደተኞችን እንዲያስወጣ ስደተኞች ጠሉ ቡድን የሰጠው ቀነ ገደብ በተቃረበበት አጋጣሚ እንደሆነ አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


ስደተኞች ጠሉ ቡድን ያስቀመጠው ቀነ ገደብ በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ያበቃል፡፡


ከቀነ ገደቡም አስቀድሞም ቢሆን በውጭ ተወላጅ አፍሪካውያን ላይ ግድያ ፣ ድብደባ እና ዘረፋ ሲፈፀምባቸው እንደቆየ መረጃው አስታውሷል፡፡


ራማፎሳ ግን በስደተኞች ላይ የሚፈፀምን ጥቃት በጭራሽ አንታገስም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


በጥላቻ ጥቃቱ ስጋት ጋና ፣ ሞዛምቢክ ፣ ማላዊ እና ናይጀሪያ የተወሰኑ ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ያስወጡ አገሮች እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page