top of page

የሰላም እጦት ኢትዮጵያን በቆዳው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ያህል ገቢ እንዳታገኝ አድርጓታል ሲል የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ተናገረ።

  • 18 minutes ago
  • 2 min read

የካቲት 12/2018


የሰላም እጦት ኢትዮጵያን በቆዳው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ያህል ገቢ እንዳታገኝ አድርጓታል ሲል የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ተናገረ።


ማህበሩ ይህን ያለው ለ15 ኛ ጊዜ የሚያካሄደውን የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርኢት “ሜሴ ፍራንክፈርት” ከተሰኘ አለም አቀፍ የንግድ ትርኢት አዘጋጅ ጋር በጋራ ለማከናወን ትናንት በስካይ ላይት ሆቴል ባደረጉት ስምምነት ወቅት ነው።


በመድረኩ ላይም በፀጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ቆዳ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ ቆዳዎችን ለመሰብሰብ ባለመቻሉ በርካታ ቆዳዎች በስብሰው እንደቀሩም ተነግሯል።


በዚህ ምክንያት ኢንደስትሪዎች ማምረት የሚገባቸውን ያህል የቆዳ ውጤቶች እንዳያመርቱ ፥ ሀገርም በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል እንዳታገኝ አድርጎታል ተብሏል።


በዘርፉ የተሰማሩ ኢንደስትሪዎች እየተቸገሩ ያሉበት ሌላኛው ደግሞ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሆነም ተነግሯል።


ይህን የነገሩን የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘላለም መራዊ ናቸው።


ማህበሩ በቆዳው ዘርፍ የሚፈልገውን ያህል ውጤት እንዳይመጣ እንቅፋት ሆነዋል ካላቸው ጉዳዮች መካከል እሴት ሳይጨመር ጥሬ ቆዳ ወደ ውጭ እንዲላክ መፈቀዱ ይገኝበታል።


ይህን በተመለከተም መንግስት እሴት ሳይጨመርበት ጥሬ ቆዳ ወደ ውጭ እንዲላክ መፍቀዱ የቆዳ እጥረት ከመጋጠሙ ባሻገር ኢንዱስትሪዎችን እንደሚያዳክም እና እንደሚጎዳ አቶ ዘላለም ተናግረዋል ።


በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን አበበ በበኩላቸው በሰላም እጦት ምክንያት ቆዳዎች እንዳይሰበሰቡና በስብሰው እንዲቀሩ አድርጓል በተባለው ነገር ላይ ከቦታው የደረሰን ሪፖርት የለም ብለዋል። እስካሁንም አሰባሰቡ ላይ የፈጠረው ችግር እንደሌለ ነው የምናውቀውም ይላሉ።


እሴት ሳይጨምርባቸው የሚላኩ ጥሬ ቆዳዎችን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት አቶ ዘሪሁን ወደ ውጭ የሚላኩትን መከልከል አንችልም ብለዋል ።


በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ላኪዎች ላይ ጫና ለመፍጠር ግን በጥሬ ቆዳው ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እየጨመርንባቸው ቢሆንም መቆም ግን አልቻለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር በቅርቡ ለ15 ኛ ጊዜ የሚያካሂደው የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርኢት በቆዳው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንደስትሪዎችም የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ሀገርም በዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን አቅም ለማሳደግ ያለመ እንደሆም ተነግሯል።


የቆዳ ኢንዱስትሪው በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያስገኘ እንደሆነም ሰምተናል።


ሙሉ ዘገባውን ያንብቡ….


ፍቅሩ አምባቸው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Recent Posts

See All
አዋሽ ኢንሹራንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦችን የጉዞ የጤና ኢንሹራንስ ሽፋን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ።

የካቲት 12/2018 አዋሽ ኢንሹራንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦችን የጉዞ የጤና ኢንሹራንስ ሽፋን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ። ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቺፍ ኮሜርሺያል ኦፊሰር አቶ ለማ ያዴቻ እና የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጅባት አለምነህ በዛሬው እለት ተ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page