top of page

ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ግብርና በአማካይ ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚሆነውን እንደሚያመጣ ይነገራል።

  • 1 hour ago
  • 2 min read

መጋቢት 29/2018


ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ግብርና በአማካይ ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚሆነውን እንደሚያመጣ ይነገራል።


መንግስት ደግሞ የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ገቢውን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ እየሰራሁ ነው ብሏል።


ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን ጥራት ማረጋገጡም እኩል ትኩረት የሚሰጠው ነው የሚለው የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ወደ ውጪ የሚላኩትም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትም በጠንካራ የፍተሻ ስርአት ውስጥ እንደሚያልፉ ተናግሯል።


ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ድርሻው ከፍ ያለ እንደሆነ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።


እንደ መረጃው ዘርፉ ለጥቅል ሀገራዊ ምርት ( #GDP ) 32 በመቶ ድርሻ ያበረክታል።


ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብም እስከ 75 በመቶ የሚሆነው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋዋሪ በግብርና ተሰማርቶ የሚገኝ እንደሆነ ይጠቅሳል።


ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ እስከ 50 በመቶ የሚደርሰው ከዚሁ ዘርፍ የሚገኝ እንደሆነ ነው መረጃው የሚያሳያው።


በዓመት በአማካይ ከሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወደ ውጪ ከሚላኩ የግብርና ምርቶች ይገኛል ብሏል።


በተለይ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ይበልጥ ለማሳደግ ግብርና የማዘመን እና ምርታማነትንም የመጨመር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ መንግስት ተናግሯል።


ምርታማትን መጨመር ብቻውን ግን ከወጪ ንግድ የሚገኘወን ገቢ ለማሳደግ በቂ እንደማይሆን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ወንዳለ ሃብታሙ ይናገራሉ፡፡


በቂ ዋጋ የሚከፍል ገበያ መኖሩንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


በኢትዮጵያ ሁኔታ ይህን ስራ የሚሰራው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደሆነ ነግረውናል።


ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን በተመለከተ የሚነሳው ሌላው ጥያቄ የጥራታቸው ጉዳይ ነው፡፡


ስለዚሁ የጠየቅናቸው ዶክተር ወንዳለ የምርቶቹን ጥራት የማረጋገጡ ስራ በአገር አቀፍም ፤ በአለም አቀፍም ደረጃ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ነው ብለውናል።


ወደ ሀገርም ውስጥም የሚገቡ የግብርና ምርቶች እንዳሉ ያስታወሱት ምክትል ዳይሬክተሩ ባለሰልጣን መስሪያ ቤታቸው 50 ቅርንጫፎችን ከፍቶ የጥራት ፍተሻውን እያካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡


ክልሎችም እንዲሁ የራሳቸው የቁጥጥር ማዕከላት አሏቸው ብለዋል።


የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ከአለም የምግብና እርሻ ድርጅት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የነገሩን ዶክተር ወንዳለ በዚህ ምክንያት ስለ ዓለም አጠቃላይ የገበያ ስርአት ያውቃል ብለዋል።


ይህም ደረጃቸውን የጠበቁ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።


ንጋቱ ረጋሣ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page