‘’የበጋው መብረቅ’’ ሌተና ጀነራል ጃገማ ኬሎ
- 2 hours ago
- 2 min read
‘’የበጋው መብረቅ’’ በሚል ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት ሌተና ጀነራል ጃገማ ኬሎ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት በ2009 ዓ.ም በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡
አርበኛው ጃገማ ኬሎ ጣሊያን ኢትዮጵያ በወረረችበት ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረጋቸው ይታወቃሉ፡፡
ጃጋማ ኬሎ የተወለዱት በጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንቢ ዮብዲ ወረዳ ውስጥ በ1913 ዓ.ም ነው፡፡
ጃገማ ለቤተሰቦቻቸው የመጨረሻ ልጅ ናቸው፡፡
በልጅነታቸው ወላጅ አባታቸውን በሞት በማጣታቸው ያደጉት ከአጎታቸው ጋር ነው፡፡
አደን ይወዱ የነበሩት ጃገማ የ15 ዓመት ወጣት እያሉ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረች፡፡
ታዳጊው አዳኝ ከሌሎች የኢትዮጵያ አርበኞቸ ጋር ሆነው ጫካ ገቡ፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አርበኞችን በማስተባበር ታዋቂ የጦር መሪና አስተባባሪ መሆን ቻሉ፡፡
በተለያዩ የጦር ሜዳዎች የኢጣሊያን ጦር ድል እያደረጉ አካባቢያቸውን ነፃ አድርገው ቆዩ፡፡
የኢጣሊያንን የአዲስ አለም ምሽግ የሰበረው እርሳቸው የሚመሩት አርበኛ ነው፡፡
ከአምስት ዓመት የአርበኞች ትግል በኋላ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ተባርሮ አፄ ሀይለስላሴ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ጅማ እና አካባቢው በኢጣሊያ ወታደሮች እጁ ነበሩ፡፡

ጅማ እና አካባቢውን ከጣሊያን ጦር ነፃ ለማውጣት በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር መሪነት ዘመቻ እንዲካሄድ ንጉሱ አዘዙ፡፡
ደጃዝማች ገረሱ ወጣቱ አርበኛ ጃገማ ኬሎን ፣ ይዘው እንዲዘምቱ ጠይቀው ተፈቀደላቸው፡፡
በጊዜው 3500 ጦር ይመሩ የነበሩት ጃገማ ኬሎ ደጃዝማች ገረሱ ዲኪን ቀድመው ጅማ እና አካባቢው ደረሱ፡፡
በዚያም የጣሊያን ጦር መግቢያ ፣ መውጫ አሳጥተው ፣ ሁለት ጀነራሎችን ማርከው ድል አገኙ፡፡
ጣሊያን ድል ሆኖ፣ ከኢትዮጵያ ሲባረር አርበኞች በያሉበት ቦታ ሆነው እንዲያስተዳድሩ የሚል ትዕዛዝ ሲወጣ አጋሮ ፣ ጌራ እና በደሌን እያስተዳደሩ ቆይተዋል፡፡
በ1934 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የሻለቃነት ማዕረግ ተቀበሉ፡፡
ከዚያ በኋላ ብርጌድና የክፍለ ጦር አዛዥነት በኋላም የብሔራዊ ጦር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በማዕጋቸውም ሌተና ጀኔራል ሆነዋል፡፡
በአገር ውስጥና በውጪ አገር ባሉ የስታፍ ኮሌጆች ያዛዥነት ኮርስ ተከታትለዋል፡፡
በባሌና፣ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛቶች ጠቅላይ ገዢ ሆነውም አገልግለዋል፡፡
በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ላይ ያተኮረ በርካታ ስራ ሲካሂዱ ቆይተዋል፡፡
ሌተና ጀነራል ጃገማ ኬሎ ለሀገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከአፄ ሀይለስላሴ ፣ ከተለያዩ ሀገሮች እና ድርጅቶች ኒሻን እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በተወለዱ በ96 ዓመታቸው አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ፡፡
ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ከሞቱ 9 ዓመት ሆናቸው፡፡
ንጋቱ ሙሉ
መጋቢት 29/2018





Comments