የሐምሌ 29 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች
- 1 hour ago
- 2 min read
በአፍጋኒስታን የተለያዩ ግዛቶች የደረሰ የጎርፍ አደጋ 29 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡
አደጋው በ130 ያህል ሌሎች ሰዎች ላይ ደግሞ አካላዊ ጉዳት ማድረሱን አናዶሉ ፅፏል፡፡
4 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል፡፡
ጎርፉ በብዙ ቤቶች እና መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት ማስከተሉ ታውቋል፡፡
በአፍጋኒስታን የተለያዩ ግዛቶች የጎርፍ አደጋው የደረሰው በዶፍ ዝናብ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በአደጋው ምክንያት ብዙ ሰዎች እርዳታ እንደሚያሻቸው ተነግሯል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት 3 ተዘዋዋሪ የጤና ባለሙያዎች ቡድኖችን በማሰማራት ድጋፍ እያደረኩ ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በየመን የውሃ ክልል በመንሳፈፍ ላይ የነበረች መርከብ ፈንጂ በተጫነ ጀልባ ተገጭታ ሰጠመች ተባለ፡፡
መርከቧ ብትሰጥም ሁሉንም 14 ባህረኞቿን ማትረፍ እንደተቻለ አለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግስት ሹሞች መናገራቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
ይሁንና ስለ ጥቃቱም ሆነ ጥቃት አድራሹን ወገን የተመለከተ በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ጥቃቱን ያደረስኩት እኔ ነኝ ያለ ወገን ብቅ አላለም፡፡
የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ ቀደም ሲል የሳውዲ አረቢያን ወደቦች በሙሉ እንከረቻችምባታለን ብለው ዝተው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
ሁቲዎቹ የውጭ አገራት መርከቦችም ራሳቸውን ከሳውዲ ወደቦች እንዲያርቁ ያስጠነቀቁት ቀደም ብሎ ነው፡፡
የሕንዷ መርከብ ፈንጂ በተጫነ ጀልባ ተመትታ የሰጠመችዋ በምን ሁኔታ እንደሆነ ለጊዜው ግልፅ አልሆነም፡፡
የአሜሪካ እና የኢራን ሹሞች በየፊናቸው የሆርሙዝ የባህር መተላፊያ ወሽመጥ ለንግድ እና ለጭነት መርከቦች ክፍት እንዲሆን ለማስቻል የሚደረገው ዲፕሎማሲዊ ጥረት እርምጃ እየታየበት ነው አሉ፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከፓራጓዩ አቻቸው ጋር ሲወያዩ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ከኢራን ጋር የሚካሄደው ድርድር መልካም እርምጃ ስለማሳየቱ መናገራቸው አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኢስማየል ባጋይ የሆርሙዝን ወሽመጥ ማስፈቻው ድርድር ጥሩ ውጤት እያስገኘ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ሆኖም ባጋይ በዚህ ጉዳይ ድርድራችን ከኦማን ጋር ብቻ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
ኢራን እና አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ በቀጥታ ስለመነጋገራቸው የታወቀ ነገር የለም፡፡
የወሽመጡ መክፈቻ ዲፕሎማሲዊ ጥረት መልካም እርምጃ አሳይቷል በመባሉ ብሬንት የተሰኘው ዓይነት የነዳጅ ዘይት ዋጋው በበርሜል ከ80 ዶላር በታች መውረዱ ተሰምቷል፡፡
የኢራኑን ጦርነት ተከትሎ የሚካሄዱ ድርድሮች እና የሚደረሱ ስምምነቶች ወሰድ መለስ የበዛቸው እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኢራኑ ፕሬዘዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል መባሉን ሐሰት ነው አሉ፡፡
የኢራን መንግስት ተቃዋሚዎች መገናኛ ብዙሃን ፕሬዘዳንቱ ከጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ሐሚኒ ጋር በፈጠሩት ያለመግባባት የስልጣን መልቀቂያ አስገብተዋል ሲሉ በተደጋጋሚ ማውራታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
የኢራኑ ፕሬዘዳንት ስልጣን የምለቅ ቢሆን ኖሮ በግላጭ አደርገው ነበር ስልጣን የመልቀቅ ፍላጎቱም እቅዱም የለኝም ብለዋል፡፡
በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልእክቸው ከጠቅላይ መሪው ጋር እየተወዛገቡ ነው መባላቸውን በግላጭ ማስተባበላቸው ተሰምቷል፡፡
ኢራን በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ ጋር በጦር ፍጥጫ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡
ቀደም ሲል ተከባሪ መሆን ያልቻለውን እና ከአሜሪካ ጋር ተደርሶ የነበረውን የጦርነት ማስቆሚያ የመግባቢያ ስምምነት ከኢራን በኩል የፈረሙት ፔዜሽኪያን እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
_edited.jpg)
