የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥን ለውጭ ሃገራት ባለሙያዎች ክፍት እንዲያደረግ ከአለም ዓቀፍ ተቋማት ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተናገረ፡፡
- 17 hours ago
- 2 min read
ሐምሌ 13/2018
የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥን ለውጭ ሃገራት ባለሙያዎች ክፍት እንዲያደረግ ከአለም ዓቀፍ ተቋማት ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተናገረ፡፡
ቦርዱ በሃገር ቤት ያሉ ባለሙያዎችን ብቁ ሳናደርግ ዘርፉን ለውጭ ሃገራት ቢከፈት የውጭ ባለሙያዎች ማራገፊያ መሆንን ያመጣል፤ የአካውንቲንግ ዘርፍን ያቀጭጫል፤ ሃገር ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ተመልሶ ከሃገር እንዲወጣ ምክንያት ይሆናል ሲልም ይሞግታል፡፡
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በሃገር ቤት ላሉ የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች የሙያ ፍቃድ ይሰጣል፤በተሰጣቸው ፍቃድ መሰረት ህጉን ተከትለው እየሰሩ መሆኑን እየተቆጣጠረ እርምጃ የሚወስድ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሂሳብ ስራ በዘፈቀደ ነው የሚሰራው የሚለው ቦርዱ የኢኮኖሚው ዘርፍ በብዙ መንገድ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በተደረገበትና አንዳንዶቹም ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ባሉበት በዚህ ጊዜ፤ ሙያው የሚጠይቀው ብቃት ያለው ባለሙያ በዚያው ልክ ያስፈልጋል ሲል ዘርፉ የካፒታል ገበያውን ጨምሮ ቢዝነሱ እየጠየቀ ያለው የሂሳብ ባለሙያ በጥቂቱ እንኳን እንደሌለ ተናግሯል፡፡

ቦርዱ ፍቃድ የሰጣቸውን ባለሙያዎች እንዴት ነው እየተቆጣጠረ እርምጃ የሚወስደው ያልናቸው የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር፤ በኦዲተሮች በኩል ያለውን ሲያስረዱ በኢትዮጵያ ሙያዊ ብቃት ያላቸው ኦዲተሮች 230 ናቸው፤3 ዓመታትን የፈጀ ፍተሻ አድርገንባቸዋል፤በተቀመጠው የቦርዱ መስፈርት መሰረት የማይሰሩ ባለሙያዎችን ፍቃድ እስከ ማገድ የደረሰ እርምጃ ስለመውሰዳቸው ጠቅሰዋል፡፡
ፍቃዳቸውን ከመሰረዝ አስቀድሞ ግንዛቤ የመፍጠር ስራን እሰራለሁ የሚለው ቦርዱ በተለይ በቅርቡ ስራ ባስጀመረው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት በኩል እየተመዘገቡ ፕሮፌሽናል(ሙያዊ ብቃት ያለው) እንሆኑ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡
በዚህ መንገድ ሰርተን ሙያተኛውን ሙያዊ ብቃት እንዲኖረው ካላደረግን ለትልልቅ ድርጅቶች የሚቀርብ ባለሙያ ጠፍቶ የኬንያ ባለሙያዎች ይህንን ቦታ እየተኩ የመስራታቸው ነገር ቀጥሎ የዘርፉን ውድቀት ያስከትላል ብለውናል አቶ ፍቃዱ፡፡
ሁሉም የኢሳብም ሆነ የኦዲት ባለሙያ ፕሮፌሽናል(ሙያዊ ብቃት ያለው) በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ማለፍ አለበት የሚለው ቦርዱ፤የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲን ጨምሮ እነዚህን ስልጠናዎች ወደሚሰጡለት ተቋማት በመሄድ ባለሙያዎች ሙያዊ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ እድሉን ማመቻቸቱንም ቦርዱ ነግሮናል፡፡
በኢትዮጵያ ሙያዊ ብቃት ያላቸውና ቦርዱ የሚያውቃቸው የሂሳብ ባለሙያዎች 500፤ ኦዲተሮች ደግሞ 230 ብቻ ናቸው መባሉን ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7
_edited.jpg)



Comments