ከዚህ ቀደም በዶላር ተገዝቶ ወደ ሃገር ሲገባ የነበረና 3.4 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኢንዱስትሪ ምርት በሃገር ውስጥ ምርት መተካቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ፡፡
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 2 min read
ጥር 26/2018
ከዚህ ቀደም በዶላር ተገዝቶ ወደ ሃገር ሲገባ የነበረና 3.4 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኢንዱስትሪ ምርት በሃገር ውስጥ ምርት መተካቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ፡፡
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሴራሚክ ሙሉ በሙሉ በሃገር ቤት ማምረት ጀምሯልም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ከፓርላማ አባላት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ 27 በመቶ የደረሰውን የሃገሪቱን ስራ የሌለው ወጣት ወደ ስራ ለማስገባት እንደ መፍትሄ ከሚቀመጡ ሃሳቦች መካከል አንዱ የሆነው የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማስፋት ነው፤ በርካታ ሰዎችን ሊያሰማሩ የሚችሉ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የሉም፤ ያሉትም አቅማቸው ተዳክሟል የሚል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ኢንዱስትሪው ተቀዛቅዟል የሚለው ምልከታ ትክክም አይደለም፤ በአንፃሩ እድገት የታየበት ነው ብለዋል፡፡
ለእድገቱ ማሳያ ነው ያሉትን ሲጠቅሱም በተጀመረው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 2.6 ሚሊዮን የቢዝነስ ድርጅቶች አሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ 413 ሺህ ያህሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ናቸው፤ በኢንቬስተር ስም የነበሩትን በመለየትና በውጤታቸው በመለካት የብርድ፣ የመሬት አቅርቦትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በሶላር ኢነርጂ ላይ የሚሰሩ 5 ፋብሪካዎች ወደ ዘርፉ ገብተዋል እነዚህ ወደ ስራ ሲገቡ በሚቀጥለው ዓመት ከሶላር ኤክስፖርት 900ሚሊዮን ዶላር እናገኛለን ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የእነዚህን አዳዲስ ዘርፎች ወደ ኢንዱስትሪው መግባት ለዘርፉ መነቃቃት ማሳያ አድርገው አቅርበዋል፡፡
በመንፈቅ ጊዜ ውስጥም ከኢንዱስትሪ የሚገኘው የኤክስፖርት ገቢ በእጥፍ አድጓል፤ 3.4 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኢንዱስትሪ ምርት በሃገር ውስጥ ምርት መተካቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኤክስፖርት አምና ከነበረው በዚህ ዓመት መጨረሻ በእጥር እንደሚጨምር ትንቢያ ሰጥተዋል፡፡
በየዘርፉ ካለው ከማዕድን ዘርፍ የተገኘው ገቢ በ30 በመቶ ሲያድግ፤ ብረት 36 በመቶ፤ ሲሚንቶ 28 በመቶ ማደጉን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፓርላማ አባላት ግንባታ ተቀዛቅዟል በሚል ለተነሳው ጥያቄ እነዚህ የግንባታ ግብዓቶች ፍላጎት መጨመር በርካታ ግንባታዎች እንዳሉ ያሳያል፤ ነገር ግን ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለግንባታ የሚውለውን ሴራሚክ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ በሃገር ቤት ማምረት ጀምሯል፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ መስታወት በሃገር ምርት ይሸፈናል፤ የዳንጎቴ ሲሚንቶን ጨምሮ ሌሎቹንም የግንባታ ግብዓቶች በራስ አቅም ለማምረት ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህን የግንባታ ግብዓቶች በቀለለ መንገድ ገበያው ላይ እንዲገኙ በማድረግ የቤት ግንባታ ወጪን ለመቀነስ እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢንዱስትሪው፣ ግብርናው፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ማዕድንና የገጠርና ከተማ ኮሪደር ልማት በፈጠሩት እድል ባለፉት 6 ወራት ለ3.4 ሚሊዮን ሰዎች ስራ ተፈጥሯል መባሉንም ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7












Comments