ከተሰጣቸዉ የስልጣን ድንበር ተሻግረዉ የሚሰሩ ኤጀንሲዎች
- sheger1021fm
- 3 minutes ago
- 2 min read
ህዳር 23 2018
መመሪያዉ በሚጠይቀዉ፣ ህጉ በሚያስገድደዉ ልክ ሆነዉ፣ ቢሮ ከፍተዉ ሰራተኛ ቀጥረው፣ ህጋዊ ሆነዉ፣ ፍቃድ አዉጥተው፣ ሰራተኛን ወደ ውጪ ለመላክ ሃላፊነት ወስደዉ፣ ደንብ አክብረዉ በስነምግባር የሚሰሩ ኤጀንሲዎች አሉ፡፡
ነገር ግን ህጋዊ ፋቃድን ተገን አድርገው፣ የተጣለባቸዉን ሃላፊነት ወደ ጎን ትተው፣ ህግ ጥሰው፣ ደንብ ተላልፈው፣ ከተሰጣቸዉ የስልጣን ድንበር ተሻግረዉ የሚሰሩ ኤጀንሲዎች ቁጥራቸዉ ትንሽ አይደለም፡፡
በተለይም ከተፈቀደላቸዉ ሀገር ውጪ መላክ፣ በተለያዩ ህግ መተላለፎች ፍቃዳቸዉ ከተሰረዘ በኋላ መስራትና ገንዘብ መቀበል በተደጋጋሚ ኤጀንሲዎች የሚጠየቁባቸዉ ጥፋቶች እንደሆነ ይነሳል፡፡
በተለይም ኤጀንሲዎች በምንም ምክንያት ስራ ፈልገዉ ከሚሄዱ ሰዎች ብር መቀበል እንደማይችሉ በህግ ተጠቅሶ፣ በአዋጅ ሰፍሮ ቢገኝም ብዙዎቹ ግን ይህንን ህግ እንደሚተላለፉ ፖሊስ ተናግሯል፡፡

ዋና ኢንስፔክተር ሰፊዉ ህዝብ እንዳለዉ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ቢሮ በህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ወንጀሎች የምርምራ ክፍል ሀላፊ ናቸዉ፡፡
ካናዳ በነፃ እንልካለን፣ የጀርመን ቪዛ እናስልካለን፣ ወደ አሜሪካ እንሸኛለን ወደ አዉሮፓ እናሻግራለን እና የመሳሰሉ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ተደጋገሞ የሚደመጡ አጓጊ ማስታወቂያዎች ሁሉ ሀሰተኛ ናቸዉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሰራተኛ ለመላክ ስምምነት ያረገችባቸዉ 4 ሀገራት ብቻ ስለመሆናቸዉም የሚያነሱት መርማሪ ፖሊሱ ከእነዚህ ውጪ ያሉ ሁሉም ህግ ወጥ ናቸዉ ይላሉ፡፡
ቪዛ የማማከርና ሰነድ ማደራጀት የሚል ፍቃድ ተቀብለዉ ሰዉን በህገ ወጥ መንገድ የሚልኩ፣ በጎብኝ ስም ህጋዊ ፍቃድ ይዘዉ ረብጣ ብር እየተቀበሉ ከተሰጣቸው ሥልጣን ውጪ የሚሰሩ ኤጀንሲዎች ስለመኖራቸዉም ፖሊስ ይናገራል፡፡
ህጋዊ ፍቃድ ኑሯቸዉ ነገር ግን በፍቃድ ሰበብ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ዘዴዎች ህገወጥ ስራ ሲሰሩ የተገኙ ኤጀንሲዎች በፖሊስ ተይዘዉ፣ ምርመራ ተደርጎባቸዉ፣ ተከስሰዉ ጥፋተኛ ሆነዉ እስከ 25 ዓመትና እሰከ 500,000 ብር የተቀጡ ስለመኖራቸዉም መርማሪ ፖሊሱ አስታዉሰዋል፡፡
ተጓዥ መንገደኞች ለምን ህገወጡን መንገድ ይመርጣሉ ስንል ላቀረብንላቸዉ ጥያቄ አንድም ፖስፖርት በቀላሉ ማግኘት አይቻልም ሲቀጥልም ሌሎች ህጋዊ ሂዳቶች አድካሚና ዉስብስብ ናቸዉ የሚሉትን ምክንያት እንደሚያረጉ መርማሪ ፖሊሱ ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ ህገወጥ መንገዱ የሚያስከትለዉ ጠባሰ ቀላል እንዳልሆነ እና በተለይም ከዚህ ሲነሱ በደላሎች ሁሉም አልጋ ባልጋ እንደሆነ ቢነገራቸዉም ፖሊስ በምርመራዉ ማጣራት እንደቻለዉ ግን በመንገድ ላይ በሚሊየን የሚቆጠር ብር እየተጠየቁ ቤተሰቦቻቸዉ እንዲልኩ ይገደዳሉ፣ ማድረግ ካልቻሉ ይደበደባሉ፣ ይደፈራሉ፣ ባህር ላይ ይወረወራሉ፣ ላስቲክ በእሳት እየተቃጠለ ከሰዉነታቸዉ ይንጠባጠብባቸዋል ብለዋል፡፡
ዘግይቶ፣ ተረጋግቶ በህጋዊ መንገድ ብቻ መሄዱ ብቸኛዉ አማራጭ እንደሆነ ፖሊስ ምክረ ሃሳቡን አስቀምጧል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..
ገዛ ጌታሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp https://tinyurl.com/ycxjmm3s








