በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት እንዲፈቀድ ለማድረግ እንደሚሟገቱ በሃገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ ያሉ የዳያስፖራ ተወካዮች ተናገሩ፡፡
- 1 day ago
- 1 min read
ሐምሌ 21 2018
በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት እንዲፈቀድ ለማድረግ እንደሚሟገቱ በሃገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ ያሉ የዳያስፖራ ተወካዮች ተናገሩ፡፡

አላግባባ ያሉና አንገብጋቢ ናቸው ተብለው በተመረጡ 8 አጀንዳዎች ላይ ሃገራዊ ምክክር መካሄድ ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡
በምክክሩ ተሳታፊ ከሆኑ 4ሺህ ተመካካሪዎች 100 ያህሉ የዳያስፖራ ተወካዮች ናቸው፤ ከመካከላቸው ሁለቱን ምክክሩ ላይ ስላላቸው ተሳትፎ ጠይቀናቸዋል፡፡
በአባይ ጉዳይ ላይ በአረቢኛ ቋንቋ በግብፅ ሚዲያዎች የሚሰሩ ዘገባዎችን ወደ አማርኛ እየተረጎሙ በሚዲያቸው በማቅረብ የሚታወቁት ኡዝታዝ ከማል በሽር ተፅዕኖ ፈጣሪ ዳያስፖራዎችን በመወከል በምክክሩ እየተሳተፉ እንደሆነ ነግረውናል፡፡
በምክክሩ በአጀንዳነት ከተያዘው የሃገር ግንባታ ስር ካሉት ንዑሳን አጀንዳዎች አንዱ የዳያስፖራው አንገብጋቢ ጥያቄ የጥምር ዜግነት ጉዳይ ነው የሚሉት ኡዝታዝ ከማል በኢትዮጵያ ህግ እስካሁን ክልክል የሆነውን ተጨማሪ ዜግነት የማግኘት መብት እንዲፈቀድ እንደሚሟገቱ ተናግረዋል፡፡
ይህንን መፍቀድ ለዳያስፖራው የተለየ ትርጉም ነው ያለው፤ ብዙ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ለመቀየር የሚገደደው በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት ስለሚከለከል ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበርን በመወከል በምክክሩ የተገኙት አቶ አብርሃም ጥላሁን የጥምር ዜግነት ጉዳይ የዳያስፖራው የሁልጊዜም ጥያቄ ነው፤ በምክክሩ መፍትሄ ይሰጠዋል ብዬ እገምታለሁ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ዳያስፖራው እንዳይሳተፍባቸው የተከለከሉ የኢንቨስትመንት አይነቶች አሉ፤ይህም ክልከላ ተነስቶ ያለ ገደብ መስራት የሚሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚሟገቱ ነግረውናል፡፡
በምክክሩ ሁሉም ተሳታፊ ይበጃል የሚለውን ሀሳብ እያመነጨ እንደሆነ የሚናገሩት ተሳታፊዎቹ በውይይቱ የሚታየው የሀሳብ ፍጭት የተሻለ ምክረ ሃሳብ እንዲወጣ የማድረግ አቅም አለው፤ በተለይ በ10 በ10 የሚደረገው ውይይት የእያንዳንዱ ሃሳብ እንዲካተት እድል የሰጠ ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በነበረው በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከኢትዮጵያ ውጭ በ6 ሃገራት እንዲሁም በበይነ መረብ ከዳያስፖራዎች ጋር ባደረገው ውይይት ዳያስፖራውን የሚወክሉ 100 ተሳታፊዎችን መምረጡን መናገሩ ይታወሳል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...
ምንታምር ፀጋው
_edited.jpg)



Comments