top of page

ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ የተፈጠሩ የማያግባቡ ትርክቶች

  • sheger1021fm
  • 2 hours ago
  • 3 min read

ህዳር 3 2018 

 

የህዝብን ስሜት ለመሳብ እና የፖለቲካ ቅቡልነት ለማግኘት ተብለው ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ የተፈጠሩ የማያግባቡ ትርክቶች መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ተጠየቀ።

 

ትርክቱን የፈጠሩት አንዳንድ የብሄር ፖለቲካ አራማጆች እና የፖለቲካ ድርጅት መስራቾች በሰሩት ስህትት ቢፀፀቱም ትርክቱ ከእነሱ ቁጥጥር ውጪ ስለሆነ ችግሩን መፍታት እና የተከሰተውን ቀውስ ማረም እንዳልተቻለም ተነግሯል፡፡

 

ይህ የተጠየቀው የኢትዮጵያ ሞያ ማህበራት ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ታሪክ እና ትርክትን መሰረት አድርጎ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

 

በውይይቱ ላይ መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የታሪክ አጥኚው እና የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ባህሩ ዘውዴ(ፕ/ር) ትርክት ማለት ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ዓላማ ታሪክን ለውስን ወይም ለራስ ፍላጎት ብቻ አመቻችቶ ማቅረብ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

 

ባህሩ(ፕ/ር) የኢትዮጵያን ገዢ ትርክት የሚፃረሩ ትርክቶችን መነሻ ሲያስረዱ ደግሞ የአጼ ሚኒሊክን ወደ ደቡብ የአገሪቱ ክፍል የግዛት መስፋፋት መሰረት ያደረገ እንደነበር ዘርዝረዋል።

 

ree

ለዚህም ምክንያቱ አንዳንዶቹ አፄ ምኒልክ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በሚገነቡበት ሂደት ተገደልን፣ ባህላችንና ፣ ቋንቋችን ተጨቆነ የሚሉ አሉ የሚለውን ተከትሎ የመጣው ነው ብለዋል፡፡

 

ይህም የጋራችን በሆነው  የአዳዋ ድል ላይ እንኳን እንዳንግባባ ብቻ ሳይሆን ድሉ አንዴ የአንዱ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሌላው ብሔር ድል ሆነ እንዲተረክ  አድርጓል ይላሉ።

 

ትርክቱ፤ ፍትህ ፍለጋ ለነፃነት በሀገር ስሜት የተዋጉ የአገር ጀግኖችን ማለትም እነ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን በአንድ ብሄረሰብ ጥላ ስር፤ ራስ መንገሻን ደግሞ በሌላ ብሄረሰብ ጥላ ስር የመክተት ችግር መፈጠሩን የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ባህሩ ዘውዴ(ፕ/ር ) ተናግረዋል።

 

በአንድነት በህብረ ብሔራዊ ጥላ ስር ፍትህን በመፈለግ ፋንታ ወደ አዲስ ትርክት የመሄድ ነገር አለ፤ ይህ እንዲሆን ግንባር ቀደም ድርሻ የተጫወቱት ደግሞ የኤርትራ የነጻነት ግንባሮች እና የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል።

 

ይህ ትርክትም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በታሪክ አንድ ሆነው እንደማያውቁ፤ ሁለቱም ከበፊት ጀምሮ የተለያዩ አገራት እንደሆኑ አንዳንዶች ደግሞ የአክሱም ታሪክም ጭምር የኢትዮጵያ ሳይሆን የኤርትራ እንደሆነ አድርገው እንደሚያቀርቡ እና እንደሚፅፉ ባህሩ ዘውዴ(ፕ/ር )አስረድተዋል።

 

በኤርትራዊያን የተጀመረው ተፃራሪው ትርክት አድጎ በኢትዮጵያ በሚንቀሳቀሱ ነፃ አውጪ የፖለቲካ ድርጅቶች እና በተማሪዎች እንቅስቃሴ እንደተደገፈ የታሪክ አጥኚው አስታውሰዋል።

 

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጌጡ ተፃራሪ ትርክቱ መተረክ የጀመረው በጣልያን ወረራ ወቅት እና በጀርመን ሚሲዮኖች ጭምር እንደሆነ አስታውሰው ትርክቱ አድጎ  የመንግስት መዋቅር እስኪገባ ለምን ተጠበቀ ብለዋል፡፡

 

በመጨረሻዎቹ አጼ የኃይለስላሴ እና በወታደራዊ መንግስት ዘመን ለምን ያን ትርክት የመቀልበስ ስራ መስራት አልተቻለም? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

 

ተፃራሪ ትርክቱ መስፋፋት ዙርያ የውጪ ሃይሎች ሚና ምን ነበር? ሲሉም አቶ ጌጡ ተጨማሪ ጥያቄ አክለዋል፡፡

 

አቶ ተስፋዬ አየለ የተባሉ ሌላ ተሳታፊ ከአብዮቱ ንቅናቄ በኋላ ታሪክን በታሪክንቱ ከመረዳት ይልቅ በአሉታዊ ትርክት ትውልዱ እንዲጠመድ መደረጉን ተናግረዋል።

 

ይህን የሚያደርገው ደግሞ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚፈልጉ ባለስልጣናት እና ፖለቲከኞች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

 

ፖለቲከኞች ስልጣን ላይ ለመቆየት እንዲያመቻቸው አጣመው ወይም በማይሆን መንገድ ታሪክን ስለ አስቀመጡት እና ወጣቱም ይህን መንገድ በመከተሉ እዚህ ጥፋት ላይ ደርሰናል ካሉ በኋላ ታድያ ይህን ትውልድ እንዴት እንመልሰው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

 

የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ዘሪሁን የተባሉ ሌላ ተሳታፊ በበኩላቸው ትርክቶች መንግስታዊ ቅርጽ ሲኖራቸው የባሰ አጥፊ እንደሚሆኑ ተናገረው ሁሉም መንግስታት የራሱ የሆነ ትርክት ነው ይዞ የሚመጣው፤ ይህም ከግጭት አዙሪት እንዳንወጣ አድርጎናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

ይህን ችግር ለመፍታት ሁሉንም የሚያካትት ትርክት ፈጥሮ የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ የምንገዛበት ሥርዓት አያስፈልግም ወይ ?ሲሉ ጠይቀዋል፡፡  

 

በግላቸው በዚሁ ጉዳይ ላይ እንደሚሰሩ እና በርካታ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን በወቅቱ የተመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማለትም የኦነግን ፣ የሕወሃትን እና የሻብዕያን መስራቾች ማናገራቸውን የተናገሩት ሌላው ተሳታፊ ደግሞ አቶ ፋሲካ ሲደልል ናቸው፡፡

 

13 ዓመታት በኤርትራ ውስጥ ሲዋጋ የነበረ ወታደር ስለ ትርክት ጉዳይ እንዳነጋገሩ ያስተወሱት አቶ ፋሲካ ወታደሩ ኤርትራ በነበረበት ወቅት ቤት ለቤት ፍተሻ በሚደርጉበት ወቅት አጼ የኃይለስላሴን "ጭራቅ" አድርጎ የሳለ በሻብዕያ የተዘጋጀ መጽሄት ማግኝታቸውን እና በመጽሔቱ ላይ ደግሞ ኤርትራ በሙሉ ደን፣ ለም እና ሃብታም እንደነበረች ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ስትቀላቀል ድሃ መሆኗን የሚያትት ጽሁፍ የያዘ መሆኑን እንደነገራቸው አስተውሰዋል፡፡

 

ይህም የህዝቡን ድጋፍ ለማግት እንዳስቻላቸው የተናገሩት አቶ ፋሲካ የኢትዮጵያም ብሄረሰብ ድርጅቶች አጀማመር እንዲሁም እድገት ከሻዕብያ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ታድያ እነዚህ ትርክቶ፤ የፖለቲካ እና የስልጣን ባለቤት ጥያቄዎች አሏቸው የሚሉት ተሳታፊው ሃሳቡን ሲያራምዱ የነበሩት እና በማራመድ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ማለትም ኦነግ፣ ሕውሃት እና ሻብያ ካልተሳተፉበት ካለመኑበት ትርክቱን ማስቀረት እና የአገሪቱን ችግር መፍታት እንደሚቸግር አስረድተዋል::

 

ተፃራሪው ትርክት ለምን በወታደራዊ መንግስት ደርግ ዘመን ማስቀረት አልተቻለም በሚል ከአቶ ጌጡ ለቀረበላቸው ጥያቄም ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ሲመልሱ በደርግ ጊዜ መንግስት በራሱ የሚያራምደው ትርክት ገዢውን ነው ብለዋል።

 

ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) የተዛባ ትርክቱ መነሻ የተማሪዎች ንቅናቄ ይሁን እንጂ የተባባሰው እና ህጋዊ የሆነው በኢሕአዴግ ዘመን መሆኑን አንስተዋል።

 

በሀሰት ትርክቱ ፈጠራ ላይ የምዕራባውያን ሚና ምን ነበር? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ጣሊያኖች በሰሜኑ ክፍል አስቀድመው ከፋፍለው ለመግዛት የሚመቻቸውን ትርክት መፍጠራቸውን እንዲሁም ደግሞ ጀርመኖች በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ለምሳሌ በወለጋ አካባቢ ተመሳሳይ ስራ ስርተዋል ብለዋል።

 

በአቶ ፋሲካ ሲደልል ሃሳብ እንደሚስማሙ የተናገሩት ባህሩ(ፕ/ር) ከገዢው ትርክት ተቃራኒ የሆኑ ትርክቶችን በመፍጠር እና በማስፋፋት ረገድ የፖለቲካ ድርጅቶች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።

 

ተፃራሪ ትርክትን ሲያራምዱ እና ሲሰብኩ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት መስራቾች መፀፀታቸውን የሚናገሩት አጥኚው ትርክቱ ግን በማህበረሰቡ ውስጥ በመስረጹ በቀላሉ መጥፋት እንደማይችል ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማህበር በአገሪቱ የማያግባቡ ትርክቶች በአገራዊ ምክክር  እንዲፈቱ አጀንዳ አድርጎ ለኮሚሽኑ ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

 

አካታች አይደለም በሚል የተቋረጠው የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታሪክ ትምህርትም ሁሉን እንዲካትት ተደርጎ ዳግም እንዲሰጥ መደረጉንም  የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ጠቁመዋል፡፡

 

ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page