top of page

''ከማህበረሰቡ ከሚቀርቡለት የተበደልን አቤቱታዎች 35 በመቶዎቹ እኔን የሚመለከቱ አይደሉም'' እምባ ጠባቂ ተቋም

  • sheger1021fm
  • 15 hours ago
  • 1 min read

ጥቅምት 26 2018

የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ከማህበረሰቡ ከሚቀርቡለት የተበደልን አቤቱታዎች 35 በመቶዎቹ እኔን የሚመለከቱ አይደሉም አለ፡፡


በህግ የተሰጠኝ ሃላፊነት የግልም ሆነ የመንግስት ድርጅቶች ማህበረሰቡ ላይ የሚፈፅሟቸውን አስተዳደራዊ በደሎች የተመለከቱ አቤቱታዎችን ተቀብሎ በመመርመር የተበዳዮችን እምባ ማበስ ነው የሚለው ተቋሙ፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሚቸገርበት ጉዳይ ማህበረሰቡ ወደ እምባ ጠባቂ ተቋም ማምጣት ያለበትን ጉዳይ አለማወቅ እንደሆነ ነግሮናል፡፡


በዚህ ምክንያት አጠቃላይ አቤቱታዎች 35 በመቶዎቹ አይመለከቱንም ብለን የምንመልሳቸው ናቸው ያሉን የተቋሙ ምክትል እምባ ጠባቂ ዶክተር የኔነህ ስመኝ ናቸው፡፡


በህዝብ ምርጫ የተቋቋሙ ምክር ቤቶች በህግ አውጪነታቸው የሚሰጧቸው ውሳኔዎችን፤ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያሉና ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች፤በዋና ኦዲተር እየታዩ ያሉና ውሳኔ የተሰጣቸው ጉዳዮች፤ በመከላከያ ሰራዊትና በፀጥታ አካላት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ተቋሙ መቀበልም ይሁን መፍትሄ ማሰጠት እንደማይችል እወቁት ተብሏል፡፡


የማይመለከተንን አቤቱታ በመቀበል ከተጠመድን የሌሎች አቤት ባዮችን ጊዜ ይሻማል የሚሉት ምክትል ዋና እምባ ጠባቂው የሚቀርቡና የማይቀርቡ ጥያቄዎችን ለማህበረሰቡ የማስረዳት ሃላፊነት ብለውናል፡፡


ተቋሙ ከተጠቀሱት ውጭ የሆኑ ማንኛውም አስተዳደራዊ በደሎችን ተቀብሎ በማጣራት በዳይና ተበዳይ ጉዳዩን በስምምነት እንዲጨርሱት ማድረግ የመጀመሪያው ስራ መሆኑን የሚያስፈዱት ዶክተር የኔነህ፤ በዚህ መንገድ ማለቅ ካልቻለ ነው ወደ ቀጣዩ እርምጃ የሚኬደው ነገር ግን ቅሬታ የቀረበባቸው ተቋማት የፈጠሩትን ችግር ለማስተካከል ፍቃደኛ አለመሆን የስራው እንቅፋት ነው ይላሉ፡፡


ከሚቀርቡለት አቤቱታዎች በተጨማሪ ተቋሙ በራሱ ተነሻሽነት መፍትሄ ሊያገኙ ጉዳዮችን ይገባል የሚላቸውን ጉዳዮች እንዲያጣራና መፍትሄ እንዲሰጥም ሃላፊነት ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡


በተቋሙ አሰራር መሰረት አጣርቶ ይስተካከሉ በማለት ለተቋማት የሚልካቸው ምክረ ሃሳቦች በ30 ቀናት ውስጥ ምላሽ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡


ወደ እምባ ጠባቂ የሚቀርቡ አቤቱታዎችም ከ6 ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እልባት እንደሚሰጣቸው ከሃላፊው ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page