ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ ከፀሀይ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጩ 4 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መግባቸው ተነገረ፡፡
- Feb 16
- 2 min read
የካቲት 9/2018
ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ ከፀሀይ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጩ 4 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መግባቸው ተነገረ፡፡
በሶማሌ ክልል የዲግ፣ የኑስደሪቅ፣ የጋሻሞ እና የምርቃን ከጸሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በላከልን መግለጫ ጠቅሷል፡፡
አራቱ ፕሮጀክቶች በድምሩ 1.8 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን፤ ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ 20.42 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ፣ 78 .46 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም 21 የተለያዩ አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች ተተክለዋል ብሏል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ከ9500 በላይ ደንበኞችን የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው የተባለ ሲሆን ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ እና ወጪው ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ብድር የተሸፈነ ነው ተብሏል፡፡

የዲግ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል በጀረር ዞን ዲግ ወረዳ የተገነባ ሲሆን፤ 350 ኪሎ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ፕሮጀክት ሲሆን የማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ ከ1500 በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያለው መሆኑ ተነግሮለታል፡፡
በግንባታውም 3 ነጥብ 03 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር፣ 21 ነጥብ 46 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የሶስት ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኗል መባሉን ከመግለጫው ተመልከተናል፡፡
የኑስደሪቅ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በቆርሀሌ ዞን በመርሲን ወረዳ የተገነባ ሲሆን፤ 275 ኪ.ዋ በማመንጨት ከ800 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በግንባታውም 3 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር፣ 13.5 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የሶስት ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኗል፡፡
የጋሻሞ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በጀረር ዞን ጋሻሞ ወረዳ ተገንብቶ፣ አንድ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ከ6 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 10 ኪ.ሜ የመካከለኛ እና 26 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የስድስት ትራንስፎርመሮች ተከላ የተከናወነለት ነው ተብሏል፡፡
ሌላኛው የምርቃን የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም በዶሎ ዞን በምርቃን ከተማ የተገነባ ሲሆን፤ 250 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው ተብሎለታል፡፡
ፕሮጀክቱ የማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ ከ1100 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በግንባታውም 4.39 ኪ.ሜ የመካከለኛ እና 17.5 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የአራት ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኗል ብሏል፡፡
በአሁን ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ 38 የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መሆኑን የተናገረው አገልግሎቱ፤ በሶማሌ ክልል ብቻ 8 የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments