top of page

ከ200,000 ለሚልቁ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ መስክ

  • sheger1021fm
  • 3 hours ago
  • 2 min read

ህዳር 15 2018

 

ከፍተኛ ሊባል የሚችል ቁጥር ያላቸው ሴቶች በኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

 

የዘርፉ ስኬቶች ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱም ይኸው የስራ ዕድል ፈጠራ ነው።

 

እንዲያም ሆኖ የሚሰሙ አንዳንድ ቅሬታዎች አሉ ። ለተመሳሳይ ስራ እኩል ክፍያ ያለማግኘት መብት አለመከበር እና የኬሚካል አጠቃቀም ችግር ይጠቀሳሉ።

 

በኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ከተጀመረ ሃያ ዓመታት አልፈዋል።

 

በእነዚህ ጊዜያት ዘርፉ ቀላል የማይባል ዕድገት ማሳየቱን መንግስት እና በስራው የተሰማሩ ባለሃብቶች ይናገራሉ።

 

ልማቱ ሲጀመር ከ28.5 ሚሊየን ዶላር የማይበልጠው የዘርፉ የአመት ገቢ አሁን ላይ ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ መሆኑ እንደ ማሳያ ይቀርባል።


ree

 

 ከ200,000 ለሚልቁ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ መስክ መሆኑም እንዲሁ ይነሳል።

 

 ከእነዚህ 200,000 ከሚሆኑ ሰዎች  በመቶዎቹ ሴቶች እንደሆኑ ተነግሯል።

 

 ልማቱ በተለይ ለሴቶች የፈጠረው የስራ ዕድል እንደ ትልቅ ስኬት የሚወሳ ነው።

 

 የስራ ዕድል መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ ግን አንዳንድ አስተያየቶችም ሲሰጡ ይሰማል።

 

አንዱ በአበባ እርሻ ላይ የሚሰሩ ሴቶች ከኬሚካል ጋር የተገናኘ ተግባር ይከውናሉ ፤ ይሄ ደግሞ በጤናቸው ላይ ጉዳት እያመጣ ነው ፤ አልፎ ተርፎ ሴቶች የመውለድ ችግር እንዲገጥማቸው ሁሉ እያደረገ ነው የሚለው ይገኝበታል።

 

የጤና ዕክል ስለ ሚያስከትሉ ለሴቶች አይፈቀዱም የተባሉ ኬሚካሎችን ጭምር በስራ ወቅት እንዲጠቀሙ ይደረጋል ነው የሚባለው።

 

የኢትዮጵያ አበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች እና ላኪዎች ማህበር ግን ቅሬታው ትክክል እንዳልሆነ ይናገራል።

 

በማህበሩ የስርአተ ፆታና እኩልነት ክፍል ሃላፊ ወይዘሮ ዮዲት ግርማ እንደሚሉት ሴቶች ከሚሚካሎች ጋር ንኪኪ እንዳይኖራቸው የሚከለክሉ አለም አቀፍ እና፤ የኢትዮጵያ ህጎች በአበባ የእርሻ ልማቶች ስለ መከበራቸው በጥብቅ ነው ቁጥጥር የሚደረገው።

 

በአበባ እርሻዎች ለመስራት የሚቀጠሩ ሴቶች በተለያዩ መብቶቻቸው እና ግዴታዎቻቸው ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፤ በየጊዜው የማሳወቅ ስራ ይሰራል የሚሉት ወይዘሮ ዮዲት አንዱም ይህንኑ የኬሚካል አጠቃቀም የተመለከተ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

ፀረ ተባይ እና ፀረ አረም ኬሚካሎችን በአበባ እርሻ ላይ መጠቀም ጉዳቱ ለወንዶችም ጭምር እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ዮዲት፤ እንደ አማራጭ የተቀናጀ የሰብል ቁጥጥር ስርአት እንዲስፋፋ ትኩረት መደረጉን ያነሳሉ።

 

በአበባ እርሻ ላይ ከሚሰሩ ሴቶች ጋር በተገናኘ ሲነሳ የሚሰማው ሌላው ቅሬታ ከወንዶች ጋር እኩል ክፍያ አያገኙም የሚል ነው።

 

ወይዘሮ ዮዲት ግን የዘርፉ ዋና ምሰሶ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ የእኩል ክፍያ ጉዳይ ነው ብለዋል።

 

የእኩል ክፍያ ጉዳይ በመንግስትም ጭምር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ቁጥጥር የሚደረግበት እንደሆነ ሃላፊዋ ተናግረዋል።

 

የስራና ክህሎት እንዲሁም የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በየጊዜው ክትትል ያደርጉበታል ብለዋል።


 ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…

ንጋቱ ረጋሣ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page