top of page

እስራኤል ለሶማሌላንድ ይፋዊ የነፃ አገርነት እውቅና መስጠቷ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጣት፡፡

  • Dec 27, 2025
  • 2 min read

ታህሳስ 18/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች



እስራኤል ለሶማሌላንድ ይፋዊ የነፃ አገርነት እውቅና መስጠቷ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጣት፡፡


ሞቃዲሾ የእስራኤልን እርምጃ አጥብቃ ማውገዟን ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡


ከሶማሊያ በተጓዳኝ ግብፅ ፣ ቱርክ እና ጂቡቲም እስራኤል ለሶማሌላንድ የነፃ አገርነት እውቅና መስጠቷን ኮንነውታል ተብሏል፡፡


አገሮቹ የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ እወቁልን ብለዋል፡፡

ሶማሌላንድ ራሷን ከተቀረችው ሶማሊያ ከነጠለች 34 ዓመታት ሆኗታል፡፡


አለም አቀፋዊ እውቅና ባይኖራትም ከሶማሊያ በተሻለ የተረጋጋች እንደሆነች ይነገርላታል፡፡


በነፃ አገርነት ይፋዊ እውቅና ስታገኝ የእስራኤል የመጀመሪያው ሆኗል፡፡


ሶማሊያ እና አጋሮቿ ሌሎችም የእስራኤልን ፈለግ እንዳይከተሉ መስጋታቸው ተጠቅሷል፡፡


እስራኤል እና ሶማሌላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚመሰርቱ ታውቋል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የሶማሌላንዱ ፕሬዘዳንት አብዱራህማን ሞሐመድ አብዱላሂን እስራኤልን እንዲጎበኙ መጋበዛቸው ተሰምቷል፡፡



የማሌዥያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛቅ የ15 ዓመታት እስር ተፈረደባቸው፡፡

ራዛቅ ለ15 ዓመታት የእስር ቅጣት የተዳረጉት በአስተዳደር ዘመናቸው ፈፅመውታል በተባለ ምዝበራ እና አድርሰውታል በተባለ ብልሹ አሰራር በፍርድ ቤት ጥፋተኛ በመባላቸው ነው፡፡


ናጂብ ራዛቅ በግላቸው ከብሔራዊ ሐብት አስተዳዳሪው መስሪያ ቤት ካዝና የ569 ሚሊዮን ዶላር የምንዛሪ ግምት ያለው ገንዘብ መዝብረዋል መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የማሌዥያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀደም ሲል በሌላ ጉዳይ 12 ዓመታት ተፈርዶባቸው በእስር ቤት በሚገኙበት አጋጣሚ ነው ተጨማሪው የ15 አመታት እስር የተደረሰባቸው፡፡


ራዛቅ የቅጣት ጊዜያቸውን በቁም እስረኝነት በቤታቸው ለማሳለፍ አቤት ቢሉም ጥያቄያቸው በፍርድ ቤት ተቀባይነት እንዳላገኘ ታውቋል፡፡


በአጠቃላይ ከማሌዥያው ብሔራዊ ሐብት አስተዳዳሪ መስሪያ ቤት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መመዝበሩን መርማሪዎች እንደደረሱበት መረጃው አስታውሷል፡፡



የሱዳኑ RSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የመንግስት ጦር በኒያላ ከተማ የገበያ ስፍራ የአየር ድብደባ ፈፀመ ሲል ከሰሰ፡፡


የደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ከተማ የሆነችው ኒያላ የRSF አስተዳደራዊ መቀመጫም እንደሆነች አልጀዚራ ፅፏል፡፡


የሱዳን ጦር የአየር ድብደባውን የፈፀመው በከተማዋ የነዳጅ መገበያያ ስፍራ ነው ተብሏል፡፡


በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ቃጠሎ መቀስቀሱ ተጠቅሷል፡፡


ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የሱዳን መንግስት ጦር ሆን ብሎ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ድብደባ ፈፅሟል ሲል መክሰሱ ተሰምቷል፡፡


የኒያላውን የአየር ድብደባ በሚመለከት የሱዳን መንግስት ጦር ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም፡፡



ወሰን ተሻጋሪ ግጭታቸው አገርሽቶ የሰነበተው ታይላንድ እና ካምቦዲያ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ፡፡


የተኩስ አቁሙ ወዲያው ስራ ላይ እንደሚውል AFP ፅፏል፡፡


ለግጭቱ ማገርሸት ታይላንድ እና ካምቦዲያ በአንቺ ነሽ አንቺ ነሽ ሲካሰሱ ሰንብተዋል፡፡


ቀደም ሲል የሁለቱ አገሮች መሪዎች በአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አቀራራቢነት የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም ስምምነቱ የሳምንት እድሜ ሳያስቆጥር ተሰናክሏል፡፡


ሁለቱ አገሮች ወቅታዊውን ግጭት ለማቆም ስለመስማማታቸው የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው ተሰምቷል፡፡


የሁለቱ አገሮች ወሰን ተሻጋሪ ግጭት አገርሽቶ በነበረበት ወቅት በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የወሰን አካባቢ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
የሐምሌ 23 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ግብፅ በግብፅ የሜዴትራኒያን የባህር ዳርቻ የነበረ የአሜሪካ የጋዝ ማጠራቀሚያ መርከብ በድሮን ተመታ ተባለ፡፡ ሁለት የደህንነት ምንጮች መርከቡ በድሮን እንደተመታ አረጋግጠውልኛል ሲል ሬውተርስ ፅፏል፡፡ መርከቡ በድሮን እንደተመታ በእሳት መያያዙ ታውቋል፡፡ ቃጠሎው ወደ ሌላ መርከብም ተጋብቶ ነበር ተብሏል፡፡ ኋላ ግን

 
 
 
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግ፣አፍሪካዊያን የጋራ መጪ እድላቸውን እንዲቀርፁ ማገዝ ያስፈልጋል ተባለ።

ሐምሌ 23 2018 የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግ፣አፍሪካዊያን የጋራ መጪ እድላቸውን እንዲቀርፁ ማገዝ ያስፈልጋል ተባለ። የአፍሪካ ሀገሮች እርስ በእርስ፣በአፍሪካና በሩሲያ እንዲሁም አፍሪካ ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳደግን ዓለማው ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተባበሩት መንግስታት የአ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page