ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ምክንያት የውጪ ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት እየመረጧት ነው ተባለ
- sheger1021fm
- Nov 14, 2025
- 2 min read
ህዳር 5 2018
ኢትዮጵያ ከወር ግድም በፊት በይፋ በተቀላቀለችው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ምክንያት የውጪ ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት እየመረጧት ነው ተባለ።
በስምምነቱ መሰረት ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ጥብቅ የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነግሮናል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ በይፋ መቀላቀሏ ይታወሳል።
ወደ አራት የአፍሪካ ሀገራት ምርቶችን በአየር እና በየብስ ትራንስፖርት በመላክ ነው የንግድ ቀጠናውን የተቀላቀለችው።
በአየር ትራንስፖርት የተላኩት ስጋ እንዲሁም የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ሲሆኑ ፤በየብስ ትራንስፖርት ደግሞ የተላኩት ቡና፣ የጥራጥሬ ምርቶችና የቅባት እህሎች ናቸው።
ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ወደ ደቡብ አፍሪካ ምርቶቹ የተላኩባቸው ሀገራት መሆናቸውም ተነግሯል።
በዚህ የስምምነት ማዕቀፍ እስከ አሁን ወደ ሀገራቱ የተላከ አጠቃላይ ምርት መጠን እና የተገኘው ገቢ ከሶስት በኋላ ተጠናክሮ ይፋ እንደሚሆን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመልክቷል።

ኢትዮጵያ የንግድ ስምምነቱን መቀላቀሏ በራሱ ግን እያመጣቸው ያሉ ውጤቶች እንዳሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ነግረውናል።
ይህን ሰፊ የአፍሪካ ገበያ ለመጠቀም የፈለጉ የተለያዩ የውጪ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት እያሳዩ ነው ብለዋል፣ የመጡም አሉ ሲሉ አክለዋል።
ለኢትዮጵያውን ሸማቾችም የንግድ ስምምነቱ የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ወንድሙ ተናግረዋል። ሸማቹ አማራጭ ምርቶችን ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ያገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከምትልካቸው ምርቶች ጋር በተገናኘ የጥራት ጥያቄ የሚያነሱ አሉ።
ወደ ነፃ ንግድ ቀጠናው ለመግባት ድርድር ሲደረግ አንዱ ቅድመ ሁኔታ የጥራት ጉዳይ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ወንድሙ ፤የጥራት መንደር የተመሰረተውም ይህንኑ ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ለመገኘት እንደሆነ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የጥራት ፍተሻ አቅም ላይ ብዙ ጥርጣሬ የለም ሲሉ አክለዋል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት 1.3 ቢሊየን የሚሆነውን የአህጉሩ ህዝብና 3.4 ትሪሊየን ዓመታዊ ምርትን የሚያስተሳስር እንደሚሆን ይገመታል።
ከአለም ንግድ ድርጅት ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ የንግድ ቀጠና እንደሆነም ተነግሯል።
54 የአፍሪካ ሀገራት ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን 27ቱ ንግዳቸውን ነፃ አድርገዋል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments