''ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የተዋዋለቻችው ሰምምነቶች ሳይተገበሩ፤ በሚዲያ ብቻ እየተወራ የሚኖረው እሰከመቼ ነው?'' የም/ቤት አባል
- sheger1021fm
- 28 minutes ago
- 2 min read
ታህሳስ 21/2018
ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ከሶማሊያ፣ ከሶማሊላንድ ጋር የተዋዋለቻችው ሰምምነቶች ሳይተገበሩ፤ አገሪቱም የባህርበር ሳታገኝ በሚዲያ ብቻ እየተወራ የሚኖረው እሰከመቼ ነው? የሚል ጥያቄ ከምክር ቤት አባል ቀረበ፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የባህር በር ጥያቄ የረጅም ጊዜ እይታ ያስፈልገዋል ፣ የማሳመን ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡
የምክርቤት አባሉ አበባው ደስአለው(ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ አጅንዳ ብቻ ሆኖ የሚቆየው እስከመቼ ነው ብለው የጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ዛሬ በፓርላማ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከምክርቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

የምክርቤት አባሉ በፈረንጆቹ 2024 ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና በሶማሊላንዱ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ መካካል የመግባብያ ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን "የባህር ባር ማግኝታችንን ሳይነገረን ፣ እኛም ለሶማሊላንድ እውቅና ሳንሰጥ አስራኤል ለመጀመርያ ጊዜ የአገርንት እውቅና ሰጥታለች ፤ኢትዮጵያ አውቅና በመስጠት ሁለተኛዋ አገር ትሆን ይሆን? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በሁለቱ አገራት ስምምነት መሰረት ሶማሊያ በማኩረፏ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የቱርኩ ፕሬዚዳንት በተገኙበት አንካራ ላይ በተደረገው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያሰረችውን ውል እንድትተው በምትኩ ከሶማሊያ የባህር በር እንድትጥቀም የሚያስችላትን አማራጭ እንድታገኝ ተነግሮ እንደነበር የጠቆሙት የምክርቤት አባሉ አበባው ደስአለው(ዶ/ር) በአራት ወራት ጊዜ ውስጥም ቴክኒካዊ ድርድሮች እንደሚጠናቀቁ ተነግሮን ነበር ብለዋል፡፡
"ነገር ግን ከሶማሊያ ጋር ያን ሰምምነትም ሆነ ከሶማሊላንድ ጋር ያለንን ውል እንዳቸውን በእጃችን ሳናስገባ ሌሎች አገራት ስምምነት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል" ሲሉ እንደራሴው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስጋት የሆነቸው ግብጽ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት እንዲሁም ከጅቡቲ ጋር ደግሞ በቅርቡ የወደብ ስምምነት፣ በተመሳሳይ ከኤርትራ ጋርም ውል ማድረጓን አስተዋውሰው "እኛስ ከአንዳቸው አገራት ጋር የተጨበጠ ወደብ ሳናገኝ በሚዲያ ብቻ እያወራን የበይ ተመልካች ሆነን የምንኖረው እስከመቼ ነው" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት ፣ ትስስር ስትራቴጂካዊ የሆነ የረዥም ጊዜ ጥቅማችንን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ለሶስት አስርት ዓመታት የነበርንብትን ሁኔታ ታውቃላቸህ ያሉት ሚኒስትሩ ይህን ለመቀልበስ እንዲሁም ለመስተካካል የረዥም ጊዜ እይታ ያስፈልጋል ሲሉ መልሰዋል፡፡
ይሄ ጉዳይ የሩብ ዓመት ግብ ሳይሆን ስትራቴጂክ የሆነ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር የአገር ግብ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ ዙሪያ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን አቋም ፣ ፍላጎት ለማስረዳት በተለያዩ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምሮ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ሚኒስትር ጌዲዮን ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ ፍልጎት እና ግብ ምንድነው የሚለውን ለአለም ማስረዳት ችለናልም ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ጌዲዮን (ዶ/ር) በፓርላማ በቀረቡበት ወቅት ኢትዮጵያ አሁን ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ምን መሳይ ነው? የሚል ጥያቄም ከእንደራሴዎች ቀርቦላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት "መልካም" የሚባል ቢሆንም በቀጠናው ባሉ አገራት ያለው የእረስ በእርስ ግጭት ግን በግንኙነቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ከአብዛኞች ጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት "ጠቅለል ባለ መልኩ መልካም የሚባል ነው" በአብዛኖቹ ጉዳይዎች ላይም ተግባብትን በጋራ የምንሰራ ነን ሲሉ መልሰዋል፡፡
"ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በቀጠናችን ያሉ ግጭቶች፣ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ያሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ በአጠቃላይ ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን በቀጠናው ባሉ አገራት እርስ በእረስ ግንኙነት ላይ የሚያጠላው ጥላ አለ" ብለዋል፡፡
ከግጭቶቹ በተጨማሪ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረው በቀጠናው ሃያላን እና መካከለኛ አገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ አይናቸወን የጣሉበት ፤የሚሻኮቱበት መሆኑ ነው ሲሉ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መክንያት "ቀጠናው ላይ የሚመጣ ጫና እና ተጽእኖ አለ" ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፡፡
እነዚህ ጫናዎች ቢኖሩም ግን ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት ከሚበዙት ጋር ጥሩ የሚባል ነው ሲሉ አስረድረዋል፡፡
ይህን ለማጠናከር በኤሌክትሪክ፣ በባቡር እና በመንገድ መሰረተ ልማት የተጀመሩ ስራዎች ይቀጥላሉ ብለዋል ጌዲዮን (ዶ/ር)፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በግንኙነቶች መካካል አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩም ተቀራርቦ በመነጋጋር እና በመወያየት መልክም የሆነው ግንኙነታችንን አጠናክረን እንቀጥላልን ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1








