ልዩ መለያ የሌላቸው ነባር ደረሰኞች ከፊታችን ጥር በኋላ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚሆኑ የገቢዎች ሚ/ር ተናገረ፡፡
- sheger1021fm
- 19 minutes ago
- 1 min read
ታህሳስ 21/2018
ልዩ መለያ ወይም ‘’ባር ኮድ’’ የሌላቸው ነባር ደረሰኞች ከፊታችን ጥር ወር በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚሆኑ የገቢዎች ሚኒስቴር ተናገረ፡፡
ከካሽ ሬጅስተር የሚወጡ ደረሰኞችንም ወደ ኤሌክትሮኒክ መላ ለመቀየር ስራ ተጀምሯል ብሏል።
ከደረሰኝ መስጠት እና መቀበል ጋር የተገናኙ ሰፋ ያሉ ችግሮች እንደሚታዩ የገቢዎች ሚኒስቴር ተናግሯል።
ሃሰተኛ ደረሰኝ ለመንግስት ማቅረብ ፤በታክስ ከፋዮች ስም ሃሰተኛ ደረሰኝ ማዘጋጀትና ያልተከፈለ የመንግስት ዕዳ አለብህ በማለት ፤ ሰዎች ላይ ያልተገባ ጫና መፍጠር ከችግሮቹ መካከል እንደሆኑ በሚኒስቴሩ የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሢሣይ ገዙ ጠቅሰዋል።
ችግሮቹን ለማስቀረት ደረሰኞች ልዩ መለያ ወይም ባር ኮድ እንዲኖራቸው ተደርገው እየታተሙ ነው ብለዋል።
እነዚህን ባለ ልዩ መለያ ደረሰኞች የማተም ስልጣን የተሰጠው ለብርሃን እና ሠላም ማተሚያ ድርጅት እንደሆነ አቶ ሢሣይ ተናግረዋል።
ነባሮቹ ደረሰኞች ከባለ ልዩ መለያዎቹ ጋር እስከ አሁን ጎን ለጎን ሲሰራባቸው እንደቆየ ሠምተናል።
ከፊታችን ጥር በኋላ ግን ነባሮቹ ደረሰኞች ሙሉ ለሙሉ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናሉ ተብሏል።

ከካሽ ሬጅስተር የሚወጡ ደረሰኞችም ችግሮች አሉባቸው ያሉት ሃላፊው ፤ እነሱንም ወደ ኤሌክትሮኒክ መላ መቀየር እንደተጀመረ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች በዚሁ እየሰሩ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በግብር ከፋዮች ማጭበርበር ተፈጽሟል ብሎ ካመነ በድብቅ መረጃ ከመሰብሰብ - ገብቶ እስከ መበርበር የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድም አቶ ሢሣይ ተናግረዋል።
የታክስ አስተዳደር አዋጁ ይህን ሰልጣን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚሰጥ ነው የጠቀሱት።
ገቢያቸውን አሳውቅው ታክስ የማይከፍሉ፤ በውሸት ከስረናል ብለው ሪፖርት የሚያደርጉ እና ተመላሽ የሚጠይቁ ነጋዴዎች አሁንም ብዙ ናቸው ሲሉ አቶ ሢሣይ ተናግረዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1








