top of page

‘’አዲስ ወደ ስራ ለሚገቡ ኢንተርፕራይዞች ብድር የሚሰጡ ተቋማት እጅግ ዝቅተኛ ናቸው’’ የኢንተርፕራይዝ ልማት ኢንስቲትዩት

  • sheger1021fm
  • 1 hour ago
  • 2 min read

ህዳር 10 2018

 

‘’አዲስ ወደ ስራ ለሚገቡ ኢንተርፕራይዞች ብድር የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት እጅግ ዝቅተኛ ናቸው’’ ሲል የኢንተርፕራይዝ ልማት ኢንስቲትዩት ተናገረ፡፡

 

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርፕራይዞች ቁጥር በሚፈለገው ልክ እንዳያድግና ዘርፉ ለውጥ እንዳያመጣ አድርጓል ተብሏል፡፡

 

የኢንተር ፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር) እንደ አፍሪካ እንኳን ቢታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንተርፕራይዞች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው ይላሉ፡፡

 

ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ቢኖርም ዋነኞቹ መንግስት በሚፈለገው ልክ አስቻይ ሁኔታ አለመዘርጋቱ ፣ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ወደ ስራ ለመግባት ድፍረት ማጣት ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ፡፡

 

ከዚህ ባለፈም ሀሳባቸውን ወደ ስራ ለማስገባት የሚጥሩ ስራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ይገጥማቸዋል ይህ ትልቁ ችግር ነው ብለዋል፡፡

 

ree

ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ስራ ሊለወጥ የሚችል ሀሳብ ላለው ሰው ብድር መስጠት ወይም የአይዲያ ፋይናንሲንግ ህግ መፅደቁ የሚታወስ ሲሆን ይህ ህጉ እስካሁን ስራ ላይ ሲተገበር እየተመለከቱ አለመሆኑን ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡

 

አንዳንድ ወጣቶች ብዙ ችግሮችን የሚቀርፍ ሀሳብ አላቸው ነገር ግን አብሯቸው የሚሰራ የፋይናንስ ተቋም እየተገኘ አይደለም በዚህ ምክንያትም ብዙዎች ስራቸውን ወደ ተግባር ሳይለውጡ ይቀራሉ ሲሉም ነግረውናል፡፡

 

አንዳንድ የፋይናንስ ተቋማት ለስራ ፈጣሪዎች ሀሳባቸውን ብቻ አምነው ብድር ለመስጠት የሚያነሱት ጥያቄ አለ እሱም ስለ ተበዳሪው ትክክለኛ መረጃ ነው ከዚህ ቀደም ይህን ችግር በወጉ የሚፈታ መላ አልነበረም ይላሉ፡፡ አሁን ግን ፋይዳ መታወቂያ ጥሩ እድል ይዞ እየመጣ ነው ብለዋል፡፡

 

በተለይ በዲጂታል ብድርና በሌሎች አማራጮች አማካኝነት ምንም ማስያዣ ለሌላቸው ወጣቶች ትክክለኛ ማንነታቸውን በማረጋገጥ ብድር መስጠት ሃሳባቸው ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚቻልበት ምህዳር መፍጠር የሚቻልበት ጊዜ እየመጣ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

 

የኢንተርፕራይዝ ልማት ኢንስቲትዩት የፋይናንስ ተቋማት ኢንተርፕራይዞች የተሻለ እድገት እንዲያሳዩና ዘርፉ እንዲያድግ ብድርና ሌሎች ድጋፎች እንዲያደርጉ ለማድረግ የማግባባት ስራ እየሰራ መሆኑን ሀሰን ሁሴን (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡

 

ከዚህ ባለፈም የአይድያ ፋይናንስ በትክክል እንደ ሀገር መተግበር ሲቻል ዘርፉ ከአሁኑ በተለየ መንገድ እድገት እንዲያመጣ ሊያደርግ ይችላልም ብለዋል፡፡

 

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…

 

በረከት አካሉ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page