አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት በማህበረሰቡ በኩል የሚሰጡ የተሳሳተ ግምቶች በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች ወደ ሃላፊነት እንዳይመጡ አድርጓል ተባለ።
- 2 hours ago
- 1 min read
የካቲት 13/2018
አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት በማህበረሰቡ በኩል የሚሰጡ የተሳሳተ ግምቶች በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች ወደ ሃላፊነት እንዳይመጡ አድርጓል ተባለ።
ይህን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።
ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አካል ጉዳተኞችን ወደ አመራርነት ቦታ እንዲመጡ፣ ውሳኔ ሰጪም እንዲሆኑ፣ በመጪው ምርጫ እራሳቸውንም እንዲወክሉ እያደረግን ነው ብለዋል።
ሆኖም በማህበረሰቡ በኩል በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች አይችሉም የሚል የተሳሳተ ግምት ስለሚሰጥ እነሱም አቅሙ ቢኖራቸውም ደፍረው ለመሳተፍ ፍቃደኛ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ተብሏል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) የድርጅት ጉዳይ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ እና የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፅሀፊ አቶ ሙሉጌታ አበበ እንደ መኢአድ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ስራዎችን እየከወን ቢሆንም በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች ውሳኔ ሰጭ እንዲሆኑ በምናደርገው ጥረት ፈቃደኞች አይሆኑም ብለዋል።
ይህም የሆነበት ምክንያት በህብረተሰቡ በኩል የሚሰጥ የተሳሳተ ግምት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ህዝባዊ አቢዮታዊ ፓርቲ(ኢህአፓ) የአካል ጉዳተኞች ዘርፍ አባል አቶ ገለታው ሙሉ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ሰፊ ስራዎች እየተከወኑ መሆኑን ነግረውናል።

አሁን ላይም አካል ጉዳተኞች ወደ መሪነት እንዲመጡ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ፓርቲዎች እየሰሩ ነው መሻሻልም እየመጣ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከአካል ጉዳተኞች ቁጥር አኳያ አሁንም ዝቅተኛ ነው ይላሉ።
በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች ወደ አመራርነት እና ወደ ውሳኔ ሰጭነት እንዳይመጡ ካደረጓቸው በርካታ ችግሮች መካከል በቂ የትምህርት ዝግጅት ስለሌላቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የወሎ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው አቶ መሐመድ ቡሩ በበኩላቸው እንደ ፓርቲ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ፖሊሲ አሰናድተን እየሰራን ነው፥ በፓርቲያችን የስራ አስፈጻሚ ቦታም እንዲሳተፉ አድርገናል ብለዋል።
ለመጪው ሀገራዊ ምርጫም ተመራጭ እንዲሆኑ እናሳተፋቸዋለን ብለውናል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ፈቅሩ አምባቸው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7












Comments