ነሀሴ 7 2017 - ''የአባይን ጉዳይ ታሪካዊ መብት” ከሚል እይታ ተላቆ የሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ልናየው ይገባል'' ዩዌሪ ሙሴቪኒ
- sheger1021fm
- Aug 13
- 1 min read
የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የአባይን ጉዳይ “ታሪካዊ መብት” ከሚል እይታ ተላቆ የሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ልናየው ይገባል አሉ፡፡
ፕሬዘዳንት ሙሴቪኒ ይህንን በኤክስ ገፃቸው ላይ የፃፉት ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በካይሮ ተገናኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡
ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በውይይታቸው ወቅት ስለ አባይ ወንዝ የወደፊት ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ሙሴቪኒ ጠቅሰዋል፡፡
የአባይን ጉዳይ ሰፋ ባለ እይታ መመልከት አለብን ያሉት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት አንዳንድ ጊዜ ችግሮች የሚያጋጥሙት ለጉዳዩ ባለን አቀራረብ ነው ብለዋል፡፡
“ታሪካዊ መብቶች” ላይ ከማተኮር ይልቅ የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች አለም አቀፍ ፍላጎትን ማጤን አለብን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ግባችን ሊሆን የሚገባው ብልፅግና ለሁሉም ፣ የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነት ለሁሉም፣ መስኖ መጠቀም ለሁሉም፣ ለሁሉም ንፁህ የመጠጥ ውሃ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህን አላማዎች በማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት ሳይንሳዊና ፍትሃዊ ዘዴዎችን ተጠቅመን ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን ሲሉ ዩዌሪ ሙሴቪኒ በኤክስ ገፃቸው ላይ ፅፈዋል፡፡

ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን በመጥቀስ በአባይ ወንዝ ላይ የተፈጥሮ እና የታሪክ መብት አለኝ አንድ ጠብታ ወሃ እንዲነካብኝ አንፈልግም በሚል በተደጋጋሚ ስትናገር ይሰማል፡፡
ግብጾች የሚጠቅሱት የቅኝ ግዛት ውልና አሁን የሚያራምዱት አቋም ለሶስትዮሹ ድርድር አለመሳካት እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪውና የህዳሴው ግድብ ድርድርን በቅርበት የሚያውቁት ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በገነባችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ድርሻን እንደማይቀንስ ይልቁንም ለቀጠናው ሀገራት ትሩፋቱ የበዛ መሆኑንን ስታስረዳ ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን የመጠቀም አለም አለም አቀፍ ህጎችም፣ የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት ያወጡት ስምምነትም አንደሚየግዟት ዶ/ር ያዕቆብ ነግረውናል፡፡
ታለቁ የህዳሴ ግድብ መስከረም ሲጠባ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments