ነሀሴ 7 2017 - ኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይትን በዲጂታል ብቻ እንዲሆን ወስና፤ ወደ ስራ ከተገባ 2 ዓመት ሞልቷል፡፡
- sheger1021fm
- Aug 13
- 1 min read
ይህም የተደረገውም የ #ነደጅ መደበቅ፣ ከተመን በላይ መስከፈል እና መሰል በዘርፉ ይታዩ የነበረው ችግሮችን ያስቀራል በሚል እንደሆነ በመንግስት በኩል ተነግሮ ነበረ፡፡
አዲሱ አሰራር በተጀመረበት 2015 የመጨረሻዎቹ ወራት በአተገባበሩ ወቅት የገጠሙ ችግሮችም ነበሩ፡፡
ተጠቃሚዎች ለአሰራሩ አዲስ መሆናቸው፣ የሲስሙ ተደራሽ አለመሆን፣ የሚተገበርበት ስርዓት ጥቂት ብቻ መሆን በወቅቱ ከገጠሙ ችግሮች የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ በዚህም በየነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም ሰለፎች ታይተው ነበረ፡፡
መንግስት ይህ ስርዓት መጀመሩ የበረከቱ ጥቅሞች አሉት፣ የነዳጅ ሌብነትም ያስቀራል ያለው አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ 2 ዓመት ቢቆጠርም አሁንም በየ ጊዜው ነዳጅ ደብቀዋል፣ ከዲጂታል ግብይት ውጪ በጀሪካን ጭምር ሲሸጡ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች እንደሚያገኝ ይናገራል፡፡
ለመሆኑ የዲጅታል የነዳጅ ስራው እንዴት እየተከውነ እንደቀጠለና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት ምን እየሰራ ነው ስንል ጠይቀናል፡፡

ይህ ስርዓት ወደ ትግበራ ከገባበት 2015 እስካሁን በጂታል መንገድ የተዘዋወረው የብር መጠንም ከግማሽ ትሪሊዮን መሻገሩን በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የብሄራዊ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ፕሮጀክት አስተባባሪ ከሆኑት ሰልማን መሀመድ ሰምተናል፡፡
በግብይት ስርዓቱ እየገጠሙ ያሉ ክፍተቶችን ጠቀሰዉ ለማሻሻል በትኩት እየሰራበት ነው ሲሉ አቶ መሀመድ ይናገራሉ፡፡
ሲጀመር በቴሌ ብር ብቻ የነበረው ግብይት አሁን ላይ የተለያዩ ባንኮች እና የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ተካትተዋል ያሉት ሀላፊው፤ የፋይናንስ ተቋማቱ እድል ተሰጥቷቸዋል መወዳደር ደንበኞችን የመሳብ ጉዳይ የራሳቸው ስራ ነው በማለትም ያስረዳሉ፡፡
ከዲጅታል ውጪ የሚሸጡ ማደያዎችን በመቆጣጠር እና እያንዳንዱ መረጃ በመከታተል እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ጠቅሰዋል አቶ ሰልማን፡፡
የነዳጅ ግብይት በዲጂታል እንዲሆን ቢወሰንም በየጊዜው መንግስት ከአሰራሩ ውጪ የሚሸጡ ማደያዎችን እያገኘ እንደሆነ ይፋ እየደረገ ነው፡፡
ለአብነትም ከ3 ሳምንት በፊት የአበአዲስ አበባ ብቻ የነዳጅ ምርት በመደበቅ እጥረት እንዲፈጠር አድርገዋል የተባሉ 3 የነዳጅ ማደያዎች መታሸጋቸውና ሰራተኞቹም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል መባሉ ይታወሳል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ……
ማንያዘዋል ጌታሁን












Comments