ነሀሴ 6 2017 - በሀላፊነት ላይ ያለ የመንግስት ሹመኛ ለክብር ዶክትሬት እንዳይታጭ የሚከለክል መመሪያ ትምህርት ሚኒስቴር አወጣ
- sheger1021fm
- Aug 12
- 1 min read
በሀላፊነት ላይ ያለ የመንግስት ሹመኛ ወይም ተመራጭ ለ #ክብር_ዶክትሬት እንዳይታጭ የሚከለክል መመሪያ የትምህርት ሚኒስቴር አወጣ፡፡
መመሪያው 8 ዙር ተማሪዎችን ያላስመረቁ እና ሶስተኛ ዲግሪ ወይም (PhD) የማያስተምሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት እንዳይሰጡ ይከለክላል፡፡
በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ሃምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ተፈርሞ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተመራው ይህ መመሪያ በቅርብ ጊዜ የተመሰረቱ የትምህርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት እንዳይሰጡ ይከለክላል፡፡

በመመሪያው ክፍል ሁለት ላይ የክብር ዶክትሬት የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስፈርትን በተመለከተ የተቀመጠው ድንጋጌ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት ለመስጠት ቢያንስ ከ8 ጊዜ በላይ ተማሪዎችን ያስመረቁ እና የሶስተኛ ዲግሪ የሚሰጡ መሆን እንዳለባቸው ያስገድዳል፡፡
በዚህም መሰረት ሰላሌ፣ ደንቢ ዶሎ፣ መቅደላ አምባ፣ ራያ፣ ደባርቅ እና መሰል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስምንት ዙር ተማሪዎችን ስላላስመረቁ በመመሪያው መሰረት የክብር ዶክትሬት መሰጠት አይችሉም፡፡
በዚሁ ክፍል ስር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ለመስጠት አገር እና አለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለባቸው ሰፍሯል፡፡
በሞያ መስኩ የተለየ ስራ ያበረከተ ከሆነ ኢትዮጵያዊም ሆነ ሌላ ዜጋ የክብር ዶክትሬት ማዓረግ ማግኘት እንደሚችል የዘረዘረው መመሪያው መስፍርቱን ካሟሉ ለግለሰብም ይሁን ለቡድን መስጠት እንደሚቻል አመላክቷል፡፡
በሕይወት ላለም ይሁን ለሌለ ሰው ማዕረጉን መስጠት እንደሚቻል የሚፈቅደው ይህ መመሪያው የክብር ዶክትሬት ለማግኘት የማይቻልባቸውን ገደቦችም በክፍል ሁለት አንቀጽ 10 ስር ዘርዝሯል፡፡
በዚህም መሰረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ የሙሉ ሰዓት ተቀጣሪ ሰራተኛ፣ የሴኔት አባላት ወይም የአስተዳደር አካላት ከተቋሙ ጋር ያላቸው ቀጥተኛ ግንኙነት እስካላበቃ ድረስ ለክብር ዶክትሬት መታጨት እንደማይችሉ ደንግጓል፡፡
መመሪያው በስራ ላይ ያሉ የመንግስት ሹሞች ወይም ባለስልጣናት ለክብር ዶክትሬት እንዳይታጩም የሚከለክል ነው፡፡
የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ግለሰብ ዶክተር፣ የክብር ዶክተር እና መሰል መጠሪያዎችን ከሰጪው ተቋም ውጪ በየትኛውም ድርጅት ውስጥ መጠቀም እንደማይችሉም ደንግጓል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በለፈው ዓመት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሽምያ የሚሰጡ የክብር ዶክትሬት ማዕረጎች መመሪያ እስኪወጣ ድረስ እንዲያቆሙ ማዘዙ ይታወሳል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments