top of page

ነሀሴ 28 2017 - በህዳሴው ግድብ ላይ እየተመረተ ያለውን የዓሣ ምርት ተረክበው የሚያከፋፍሉ ባለሃብቶች ወደ ገበያው እንዲገቡ ጥሪ ቀረበ

  • sheger1021fm
  • 5 days ago
  • 2 min read

በህዳሴው ግድብ ላይ እየተመረተ ያለውን የዓሣ ምርት ተረክበው የሚያከፋፍሉ ባለሃብቶች ወደ ገበያው እንዲገቡ ጥሪ ቀረበ፡፡


የግድቡ ግንባታ በፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ላይ በርከት ያለ የዓሣ ምርት እየተገኘ መሆኑን ሲነገር ቆይቷል፡፡


በ2017 ዓ.ም ብቻ 5,895 ቶን ዓሣ መመረቱን የዓሣ ምርቱን በበላይነት የሚቆጣጠረው ግድቡ የሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነግሮናል፡፡


ከግድቡ የሚገኘውን የዓሣ ምርት ለመላው ኢትዮጵያ መድረስ የሚችል ቢሆንም እስካሁን ሲሰራ የቆየው በተበጣጠሰ መንገድ ነው፤ ወደ ገበያ የሚያቀርቡ ባለሃብቶች ያስፈልጋሉ ተብሏል፡፡


በተጨማሪም ዓሣ በባህሪው ቶሎ የሚበላሽ በመሆኑ ማቀዝቀዣ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ማቅረብ የሚችሉ፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ አደራጅተው እንዲመረት በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚረከቡ ባለሃብቶች እንደሚያስፈልጉ ሰምተናል፡፡

ree

ይህንን ስራ ለመስራት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል የሆነው ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ በቅርቡ ወደዚህ ስራ ገብቷል ያሉን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የእንሰሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ምክትል የቢሮ ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ብርሃኔ ቱፋ ናቸው፡፡


በጉባና አካባቢው ያሉ ከ849 በላይ ወጣቶች በ72 ማህበራት ተደራጅተዋል፤ ከእነዚህም 31ዱ ወደ ዓሣ ማስገር ስራው ገብተዋል ተብሏል፡፡


ከዚህም በኋላ የሚደራጁ አምራች ወጣቶች እየተዘጋጁ ነው፤ምርቱ በደምብ አለ፤በዚህ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች ቢመጡ ከአምራቾች ጋር የማገናኘት ስራ እንሰራለን ብለውናል ሃላፊው፡፡


በስፍራው በቀን 14,000 ኪሎ ግራም ዓሣ የማምረት አቅም መፈጠሩን በቅርቡ የግብርና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡


ከህዳሴ የሚወጡ የዓሣ ምርቶች በመጠን በጣም ትልልቅ ናቸው የሚሉት ዶክተር ብርሃኔ ዓሣ አስጋሪዎቹ ያሉባቸው የማስገሪያ ቁሳቁሶች ችግሮች አሁንም እንዳልተፈቱ ጠቅሰዋል፡፡


አምራጮቹ ደጋግመው የሚያነሱትን የማስገሪያ ጀልባዎች ችግር ለመፍታት በ2017 ዓ.ም 55 ጀልባዎችን ለህዳሴ ግድብ አቅርበናል፤ ከዚህም 5ቱ የሞተር ሲሆኑ ቀሪዎቹ 50ው ጀልባዎች የእንጨት ናቸው፤ ይህም ቢሆን ካለው ሰፊ የማምረት አቅም አንፃር በቂ አይደለም ብለዋል፡፡


የግድቡ አሣ የማምረት አቅም በተለያዩ ወቅቶች ሲነገር የነበረው በዓመት 8,000 ቶን ነው የሚል ነው 22,000 ቶን በዓመት የሚል ጥናትም አለ፤ ነገር ግን አሁን ያለውን ትክክለኛ የማምረት አቅም ለማወቅ ሌላ ጥናት ያስፈልጋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡


ከቀናት በኋላ እንደሚመረቅ ከሚጠበቀው ከታላቁ የህዳሴ ግድብ በመጪው የ2018 ዓመት 9,500 ቶን ዓሣ ለማምረት ውጥን መያዙን ከሃላፊው ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page