ነሀሴ 1 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Aug 7
- 2 min read
የሊባኖሱ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት (ሔዝቦላህ) ትጥቅ እንዲፈታ በመንግስት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ጥፋት ብቻ ሳይሆን ሐጢያትም ነው አለው፡፡
በቅርቡ የሊባኖስ መንግስት የአገሪቱ ጦር ሔዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት የሚያስችለውን ዝርዝር እቅድ እንዲያሰናዳ መወሰኑን ሬውተርስ ፅፏል፡፡

የሊባኖስ መንግስት ታጣቂዎች የያዟቸው ሁሉም የጦር መሳሪያዎች በመንግስት ጦር እጅ እንዲገቡ ለማድረግ ወስኗል ተብሏል፡፡
የሺአዎች ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ በሊባኖስ ውስጥ በመንግስት ላይ ያለ ሌላ መንግስት ተደርጎ ሲቆጠር ቆይቷል፡፡
አሜሪካ የሊባኖስ መንግስት ሔዝቦላህን ትጥቅ እንዲያስፈታ ግፊቷን አበርትታበታለች ይባላል፡፡
ሔዝቦላህ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ ሸሪክ ተደርጎ ሲቆጠር መቆየቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
በምዕራብ አፍሪካዊቱ አገር ጋና በደረሰ የሄሊኮፕተር መከስከስ አደጋ ሁለት ሚኒስትሮችን ጨምሮ የስምንት ሰዎች ሕይወት አለፈ ተባለ፡፡
በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው የመከላከያ እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ለክፉ እጣ የተዳረገችው ወታደራዊ የመጓጓዣ ሒሊኮፕተር 5 መንገደኞችን እና ሶስት ሰራተኞቿን አሳፍራ ነበር ተብሏል፡፡
ሔሊኮፕተሯ የተከሰከሰችው ከርዕሰ ከተማዋ አክራ ተነስታ በአሻንቲ ግዛት ወደምትገኘው ኦቡአሲ ከተማ በማምራት ላይ በነበረችበት ወቅት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ሹሞቹ በኦቡአሲ ከተማ ህገ-ወጥ የማዕድን ማውጣትን መከላከል ባለመ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት አቅደው ነበር ተብሏል፡፡
ለጊዜው ሔሊኮፕተሯ በምን ምክንያት እንደተከሰከሰች የታወቀ ነገር የለም፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሕንድ ላይ የቀረጥ ታሪፍ ብሎናቸውን እያጠበቁባት ነው፡፡
ትራምፕ በሕንድ ላይ ሰሞኑን ከጣሉባት የቀረጥ ታሪፍ በተጨማሪ የ25 በመቶ ታሪፍ ትከፍይኛለሽ እንዳሏት ሜዱዛ ድረ ገፅ የዋይት ሐውስ ምንጮችን ጠቅሶ ፅፏል፡፡
በዚህም አሜሪካ በሕንድ ላይ የቀረጥ ታሪፍ ወደ 50 በመቶ አሻቅቧል ተብሏል፡፡
በሕንድ ላይ ተጨማሪው የ25 በመቶ የቀረጥ ታሪፍ የተጣለባት የሩሲያን ነዳጅ መግዛቷን በመቀጠሏ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
ሕንድ 2ኛዋ ታላቅ የሩሲያ የነዳጅ ሸማች አገር እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት የቀረጥ ታሪፍ እርምጃቸውን ከምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዩን አሻግረው ለፖለቲካ መሳሪያትም እያዋሉት ነው ይባላል፡፡
ህንድ የአሜሪካን የቀረጥ ታሪፍ እርምጃ ኢፍትሃዊ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ስትል እያወገዘችው ነው፡፡
በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት በሚገኝ የጦር ሰፈር አንድ የ50 አለቃ በከፈተው ተኩስ 5 ወታደሮች አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተሰማ፡፡
ጥቃት አድራሹ በሌሎች ወታደሮች ርብርብ እንደተያዘ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ተተኩሶባቸው ጉዳት የገጠማቸው ወታደሮች የህክምና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡
ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈፀም የተረባረቡት ወታደሮች በአለቆቻቸው ምስጋና እንደተቸገራቸው ታውቋል፡፡
ጥቃት አድራሹ ቀደም ሲልም የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ በማሽከርከር ታስሮ እንደነበር ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡
የሃምሳ አለቃው ጥቃት የፈፀመበት ሽጉጥ ሰራዊቱ የሚገለገልበት አይደለም ተብሏል፡፡
ስለ ጉዳዩ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s
Comments