top of page

ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችን ሥነ ምግባር ለመቆጣጠር ያዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ

  • sheger1021fm
  • 4 hours ago
  • 3 min read

ህዳር 11 2018


ሴት ተማሪዎች የጥፍር፣ የፀጉርና የከንፈር ቀለም መቀባት፣ ቅንድብ መቀንደብና መኳኳል፣ አላስፈላጊ ጌጣ ጌጦችን አድርጎ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የሚከለክል መመሪያ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጀ፡፡


ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችን ሥነ ምግባር ለመቆጣጠር ያዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ማንኛውም ተማሪዎች ከተፈጥሮ ጸጉራቸው በስተቀር አርቴፊሻል ፀጉር መቀጠል አይችሉም ተብሏል፡፡


ከዚህ ባለፈም በትምህርት ቤት ውስጥ አላስፈላጊ የሆኑ የኢትዮጵያዊነት ባህልን የማይገልፁ በዓላት በተለይም እንደ ክሬዚ ዴይ፣ ኦልድ ዴይ፣ ቤቢ ዴይ፣ ቶማቶ ዴይ፣ ከለር ዴይ፣ ቫላንታይን ዴይ እና ሌሎችም የበዓል ቀናቶች ተብለው የሚከበሩ በዓላት ማክበር በመመሪያው ተከልክሏል፡፡


በትምህርት ቤት የደንብ ልብስ በተገቢ መንገድ መልሰብ ሲል ባወጣው መመሪያ ስር ሴቶች ጉርድ ቀሚስ ከባት በታች የሆነ ቁመት ያለው ለብሶ መገኘት አለባቸው ተብሏል፡፡


ከደንብ ልብስ ውጪ ቢሆን ከአካባቢው ባህል ጋር የማይቃረን አለባበስ መልበስ ይጠበቅባቸዋል ይላል ረቂቅ መመሪያው፡፡


ትምህርት ቤት ውስጥ መፈፀም የተከለከሉ ድርጊቶች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል ደግሞ የትምህርት ቤቱን መምህራን፣ የትምህርት አመራር፣ ሠራተኞችና ሌሎች የትምህርት ማህበረሰብ አካላትን መዝለፍ፣ መስደብ፣ ማንቋሸሽና አካላዊ ጥቃት መፈጸም ቅጣት የሚያስከትል ተግባር ነው ተብሏል፡፡


ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም ሞባይል እና የሙዚቃ ማዳመጫ መሣሪያዎችን ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ይዞ መገኘት ረቂቅ መመሪያው ከልክሏል፡፡

ree

በቃል፣ በምልክትም ሆነ በጽሑፍ ፀያፍ ነገሮችን መግለፅ፤ ጨዋነት የጎደላቸውን እንዲሁም ሐይማኖታዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ምስሎችና ጽሑፎች በትምህርት ቤት ውስጥ ይዞ መገኘትና ማሰራጨት አይፈቀድም፡፡


በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የማንኛውንም ዓይነት የኃይማኖት አምልኮ ሥርዓትና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ ይከለክላል፡፡


ማንኛውም ተማሪ አገራዊ እሴት ያልሆኑና መጤ የሆኑ ነገሮችን በሰውነት ላይ ምልክት ማድረግ፤ ከአገራዊ እሴት ጋር የሚቃረኑ አሉታዊ መጤ ምልክቶችን በሰውነት ላይ መነቀስ፣ ማሳየት፣ ማድረግ፣ መጠቀም ፍፁም የተከለከለ ነው ብሏል ረቂቅ መመሪያው፡፡


ከ9 እስከ 12ተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች አንድ ተማሪ በሥነ-ምግባር ጉድለት እጅ ከፍንጅ ከተያዘና የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያውክ ሆኖ ከተገኘ ውሳኔ እስኪሰጠው ከትምህርት ቤት ሊታገድ እንደሚችልም በመመሪያው ሰፍሯል፡፡


ተማሪዎች ተደጋጋሚ ጥፋት አጥፍተው ሲገኙ በተለይም ከ7 እስከ 12ተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች እስከ 1 ዓመት ድረስ እንደ ጥፋቱ መጠን ታይቶ ከትምህርት ሊታገዱ ይችላልም ሲል ረቂቅ መመርያው አስቀምጧል፡፡


በሌላ በኩል በትምህርት ቤቶችና አካባቢ የትምህርት አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ረቂቅ ደንብ ተሰናድቷል፡፡


በዚህ ረቂቅ ደንብ ትምባሆ(ሲጋራ፣ ሺሻ)፣ ጫት፣ አልኮል የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ ዝርያ ያላቸው አደገኛ ህገ ወጥ መድኃኒቶች እና ሱስ አስያዥ ዕፆች ትምህርት ቤት አካባቢ መሸጥም ሆነ ይዞ መገኘትን ይከለክላል።


የአልኮል መሸጫ እና ማከፋፈያ ቤቶች፣ የሲጋራ መሻጫ ሱቆች፣ ሺሻ ቤቶች፣ ጫት መሸጫና መቃሚያ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፤ ቁማር ቤቶች፤ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች እና የሰውነት መታሻ ወይም ማሳጅ ቤቶች በትምህርት ቤቶች በ500 ሜትር ርቀት ውስጥ መክፈት አይቻልም፡፡


ፊልም ማጫዎቻ ቤቶች፣ ፕሌይ ስቴሽን ቤቶች፣ ዲ.ኤስ.ቲቪ ቤቶች፣ ከረንቡላ፣ ፑል፣ ጆተኒ፣ ቢንጎ እና የስፖርት ቁማር መጫወቻ ቤቶችም በትምህርት ቤት አቅራቢያ መክፈትን ከልክሏል።


ከትምህርት አዋኪ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የንግድ ዘርፎች ላይ ንግድ ፈቃድ ሲሰጥ ከትምህርት ተቋማት ከ500 ሜትር ርቀት በኋላ መሆናቸውን መረጋገጥ አለበት ብሏል ረቂቅ ደንቡ፡፡


የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ከሚጠቀምባቸው ተሽከርካሪዎች በስተቀር ተሽከርካሪ ማቆም፣ ማሳደር፣ ተሽከርካሪ እጥበት እና የጋራጅ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ መሆኑን በደንቡ ላይ ተቀምጧል፡፡


ማንኛውም ትምህርት ቤት አዋኪ ድርጊት ከሚፈጸምባቸው ስፍራ እርቆ መቋቋም አለበት ሲል አስቀምጧል፡፡


በረቂቅ ደንቡ መሰረት የጫት መሸጫና መቃሚያ የከፈተ 50,000 ብር ፣ የሺሻና ሲጋራ መሸጫና ማስጨሻ የከፈተ 100,000 ብር፣ ፊልም ወይም ቪዲዮ ቤት የከፈተ 20,000 ብር ፣ የቀንም ሆነ የሌሊት ጭፈራ ቤት የከፈተ 100,000 ብር ፣ ማንኛውም ዓይነት የአልኮል መጠጥ መሸጫና መጠጥ ቤት የከፈተ ከ10,000 ብር እስከ 20,000 ብር ይቀጣል፡፡


ማንኛውንም ዓይነት ቁማር ቤት የከፈተ 150,000 ብር ፣ የእንግዳ ማረፊያ ቤት የከፈተ 100,000 ብር ፣ የሰውነት መታሻ ወይም ማሳ ቤት የከፈተ 150,000 ብር ፣ የትምህርት አዋኪ ጉዳዮችን ለሚፈፅሙ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ንብረታቸውን የሚያከራዩ 30,000 ብር ይቀጣሉ ተብሏል፡፡


ይህ ደንብ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ትክክለኛውን ርቀት ሳይጠብቁ በትምህርት ቤትና አካባቢ የተከፈቱ የትምህርት አዋኪ ተብለው የተጠቀሱ የመጠጥና ሌሎች የንግድ ቤቶች ላይ ደንቡ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን የማስተካከያ ጊዜን እና የማካካሻ ጉዳይን በተመለከተ በዝርዝር መመሪያ የሚወሰን ይሆናል ሲል ደንቡ ተጠቅሷል፡፡


በረከት አካሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page